ኢትዮጵያን በጠንካራ የኢኮኖሚ መሠረት ላይ ለማጽናት ለአምራች ኢንዱስትሪው ዘርፍ ትኩረት ተደርጓል - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያን በጠንካራ የኢኮኖሚ መሠረት ላይ ለማጽናት ለአምራች ኢንዱስትሪው ዘርፍ ትኩረት ተደርጓል
አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 18/2018 (ኢዜአ)፡- መንግሥት ኢትዮጵያን በጠንካራ የኢኮኖሚ መሠረት ላይ ለማጽናት ለአምራች ኢንዱስትሪው ዘርፍ በትኩረት እየሠራ መሆኑን የኢንዱስትሪ ሚኒስትር መላኩ አለበል ገለጹ።
የኢትዮጵያ ታምርት የ10 ኪሎ ሜትር የጎዳና ላይ ሩጫ በአዲስ አበባ መስቀል አደባባይ ተካሂዷል።
ሚኒስትር መላኩ በዚሁ ወቅት፤ የሩጫ ውድድሩ ገቢ ምርትን በመተካት የተሰማሩ አምራች ኢንዱስትሪዎች የስፖርት አልባሳትን ማስተዋወቅ እና የማምረት ዐቅማቸውን ለማሳየት ያለመ መሆኑን ተናግረዋል።
መንግሥት ባለፉት የለውጥ ዓመታት ኢትዮጵያን በጠንካራ የኢኮኖሚ መሠረት ላይ ለማጽናት ለአምራች ኢንዱስትሪው ዘርፍ ልዩ ትኩረት ሰጥቶ ሲሠራ መቆየቱንም አስረድተዋል።
በዚህም በአምራች ዘርፉ በርካታ አመርቂ ውጤቶች መመዝገባቸውን ጠቁመው፤ በተለይም የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ ከተጀመረ ወዲህ ዘርፉ ከፍተኛ መነቃቃት እንደታየበት አንስተዋል።
በአሁኑ ወቅት ምርቶች በጥራትም ሆነ በመጠን እየተመረቱ እንደሚገኝ የገለጹት ሚኒስትሩ፤ የዜጎች የሀገር ውስጥ ምርትን የመጠቀም ባህል ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ መምጣቱን አመላክተዋል።
ከውጭ ይገቡ የነበሩ ምርቶችንም በሀገር ውስጥ መተካት መቻሉን አአረጋግጠዋል።
በቀጣይም ዘርፉ ለሀገር ኢኮኖሚ የሚያበረክተውን አስተዋጽኦ ይበልጥ ለማሳደግ መንግሥት በትኩረት እንደሚሠራ ተናግረዋል።
የባህልና ስፖርት ሚኒስትር ሸዊት ሻንካ በበኩላቸው፤ መንግሥት ብቁና ንቁ ትውልድ ለመገንባት ለስፖርት ዘርፍ ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
በዚህም ባለፉት የለውጥ ዓመታት የስፖርት መሠረተ-ልማቶችን በማስፋፋት ለስፖርት ማኅበረሰቡ ሰፊ ዕድሎች መፍጠሩን ነው ያመላከቱት።
ስፖርቱንና የኢንዱስትሪውን ዘርፍ በማቀናጀት የስፖርት ትጥቆች በሀገር ውስጥ ምርቶች እንዲተኩ እየተደረገ መሆኑንም አስታውቀዋል።
በተፈጠረው ቅንጅትም የዛሬው የ10 ኪሎ ሚትር የኢትዮጵያ ታምርት ሩጫ ውድድር አልባሳት በኢትዮጵያ የተመረቱ መሆናቸውን ነው የተናገሩት።
ከለውጡ ወዲህ በአዲስ አበባ የኢንዱስትሪ ዘርፍ ከፍተኛ እመርታ አምጥቷል ያሉት ደግሞ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ እና የኢንዱስትሪ ልማት ቢሮ ኃላፊ ጃንጥራር ዓባይ ናቸው።