የመደመር መንግሥት ቅርሶቻችን የሀገር ኩራት እንዲሆኑ የጀመረውን ሥራ አጠናክሮ ይቀጥላል - ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ - ኢዜአ አማርኛ
የመደመር መንግሥት ቅርሶቻችን የሀገር ኩራት እንዲሆኑ የጀመረውን ሥራ አጠናክሮ ይቀጥላል - ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ
አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 18/2018 (ኢዜአ)፡- የመደመር መንግሥት የታሪክ ሥፍራዎችን መልሶ በማልማት ቅርሶቻችን የሀገር ኩራት እንዲሆኑ የጀመረውን ሥራ አጠናክሮ ይቀጥላል ሲሉ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ገለጹ።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማኅበራዊ ትስስር ገጻቸው ባስተላለፉት መልዕክት፤ ኢትዮጵያ የረጅም ዘመናት ሥልጣኔና የጥንታዊ ቅርሶች ባለቤት መሆኗን የምንመሰክረው እንደ አቶ አብዲ ዓይነት የትውልድ ዐሻራ ጠባቂዎችን ስንመለከት ነው ብለዋል።
አብዲ ነጋሽ ቅርስ ማሰባሰቢያና ማስጎብኛ ቤት ተገኝተን የጎበኘነው የቅርሶች ስብስብ፤ ለሀገራችን ታሪክና ባህል ትልቅ ክብር የሚሰጥ ድንቅ ሥራ ነው ሲሉም ገልጸዋል።
እነዚህ ሀብቶች፤ አሁን በሚመጥናቸው ታሪካዊ ሥፍራ ተደራጅተው ለዕይታ መብቃታቸው ለዘርፉ ትልቅ እመርታ ነውም ብለዋል።
ትውፊታዊ ቅርሶቹ ባለፈውና በሚመጣው ትውልድ መካከል የቆሙ ኅያው ድልድዮች መሆናቸውንም ተናግረዋል።
የኢትዮጵያን ዕምቅ ዐቅሞች በመግለጥ ረገድ ግለሰቦች የማይተካ ሚና እንዳላቸውም ነው የገለጹት።
እንደ አቶ አብዲ ዓይነት በፍላጎት እና በሀገር ፍቅር ስሜት የሚሠሩ ሰዎች ደግሞ የዜጋን አስተዋጽዖ ይበልጥ ከፍ ያደርጋሉ ብለዋል።
የአቶ አብዲ የቅርሶች ስብስብ የከተማችን አንዱ የቱሪስት መስሕብ ሆኗል፤ የቅርስ ዜጋዊ ዲፕሎማሲ ማሳያም ነው ብለዋል በመልዕክታቸው።
አያሌ የሀገር ውስጥና የውጭ ቱሪስቶች በየጊዜዉ ይጎበኙታል ሲሉም አመላክተዋል።
እንዲህ ያሉ የሀገር መዝገቦችን በታሪካዊ ሕንጻዎች ውስጥ ጠብቆ ማቆየት፣ ለብልጽግና የምናደርገውን ጉዞ በዕውቀትና በማንነት ላይ ለመገንባት የሚያግዘን ተደማሪ ዐቅም ነው ሲሉም አስገንዝበዋል።
የመደመር መንግሥት እንደነዚህ ያሉ የግል ጥረቶችን በማበረታታትና የታሪክ ሥፍራዎችን መልሶ በማልማት፣ ቅርሶቻችን የኢኮኖሚ ምንጭና የሀገር ኩራት እንዲሆኑ የጀመረውን ሥራ አጠናክሮ ይቀጥላል ሲሉ አረጋግጠዋል።
ተቋማትና ሀገር ወዳድ ዜጎች እንደ አቶ አብዲ ያሉ ታታሪዎችን እንዲደግፉም ጥሪ አቅርበዋል።