የኢትዮጵያ ታምርት የ10 ኪሎ ሜትር የጎዳና ላይ ሩጫ እየተካሄደ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ ታምርት የ10 ኪሎ ሜትር የጎዳና ላይ ሩጫ እየተካሄደ ነው
አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 18/2018 (ኢዜአ)፡- የአምራች ኢንዱስትሪዎችን የስፖርት አልባሳት ማስተዋወቅ እና የማምረት ዐቅማቸውን ለማሳየት ያለመ የ10 ኪሎ ሜትር የጎዳና ላይ ሩጫ በአዲስ አበባ መስቀል አደባባይ እየተካሄደ ነው።
የጎዳ ላይ ሩጫውን የኢንዱስትሪ ሚኒስትር መላኩ አለበል፣ የባህልና ስፖርት ሚኒስትር ሸዊት ሻንካ፣ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ እና የኢንዱስትሪ ልማት ቢሮ ኃላፊ ጃንጥራር ዓባይ፣ የኢትዮጵያ አትሌትክስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት ኮማንደር አትሌት ስለሺ ስኅንን ጨምሮ ሌሎች የመንግሥት ሥራ ኃላፊዎች አስጀምረውታል።
የሩጫ ውድድሩ ገቢ ምርትን በመተካት የተሰማሩ አምራች ኢንዱስትሪዎች የስፖርት አልባሳትን ማስተዋወቅ እና የማምረት ዐቅማቸውን ለማሳየት ያለመ ነው።
ዜጎች የሀገር ውስጥ ምርትን የመጠቀም ባህል እንዲያሳደጉ ግንዛቤ የሚፈጠርበት መሆኑንም ተገልጿል።
ውድድሩ አዲስ አበባ ከተማ ያላትን የቱሪዝም ሀብት ለማስተዋወቅ ተደማሪ ዕድል ይፈጥራልም ተብሏል።
በውድድሩ በርካታ ተሳታፊዎች የተገኙ ሲሆን፤ ከነዚህ ውስጥ 500 የሚሆኑት ኢሊት አትሌቶች ናቸው።
በዚህ ውድድር በሁለቱም ጾታዎች አሸናፊ ለሚሆኑ ተወዳዳሪዎች ጠቀም ያለ ሽልማት መዘጋጀቱ ተገልጿል።
የጎዳና ላይ ሩጫው ለአትሌቶች አዲስ የውድድር ዕድል እንደሚፈጥርም ነው የተመላከተው።