ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ ቡና እና ቅዱስ ጊዮርጊስ 52ኛው የፕሪሚየር ሊግ የደርቢ ጨዋታ ይጠበቃል

አዲስ አበባ፤ ሚያዚያ 18/2018 (ኢዜአ):- በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የ20ኛ ሳምንት ተስተካካይ መርሐ ግብር ኢትዮጵያ ቡና እና ቅዱስ ጊዮርጊስ የሚያደርጉት የደርቢ ጨዋታ የእግር ኳስ አፍቃሪያንን ቀልብ ስቧል። 

የሁለቱ ክለቦች ጨዋታ ከቀኑ 9 ሰዓት በአዲስ አበባ ስታዲየም ይካሄዳል። 

ኢትዮጵያ ቡና በሊጉ እስከ አሁን ባደረጋቸው 27 ጨዋታዎች በ10ሩ ድል ሲቀናው በዘጠኙ ሽንፈት አስተናግዷል። በቀሪ ስምንት ጨዋታዎች አቻ ተለያይቷል።

ቡናማዎቹ በጨዋታዎቹ ላይ 28 ግቦችን ሲያስቆጥር በተመሳሳይ 28 ጎሎችን አስተናግዷል። ቡድኑ በ38 ነጥብ ሰባተኛ ደረጃን ይዟል።  

ተጋጣሚው ቅዱስ ጊዮርጊስ በውድድር ዓመቱ 27 ጨዋታዎችን አድርጎ በዘጠኙ ሲያሸንፍ በ10ሩ ሽንፈት አስተናግዷል። በቀሪ ስምንት ጨዋታዎች አቻ ወጥቷል።

በ27ቱ ጨዋታዎች 23 ግቦችን ሲያስቆጥር 24 ጎሎችን አስተናግዷል። ቅዱስ ጊዮርጊስ በ35 ነጥብ 10ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል።

ቡድኖቹ በሊጉ እርስ በእርስ ሲገናኙ የአሁኑ ለ52ኛ ጊዜ ነው።

ከዚህ ቀደም 51 ጊዜ ተጫውተው ቅዱስ ጊዮርጊስ 22 ጊዜ በማሸነፍ የበላይነቱን ሲይዝ ኢትዮጵያ ቡና 9 ጊዜ ድል ቀንቶታል። 20 ጊዜ ደግሞ አቻ ተለያይተዋል።

በ51ዎቹ ጨዋታዎች በድምሩ 98 ጎሎች የተቆጠሩ ሲሆን ቅዱስ ጊዮርጊስ 64 እንዲሁም ኢትዮጵያ ቡና ደግሞ 34 ግቦችን ከመረብ ላይ አሳርፈዋል።

ኢትዮጵያ ቡና የሊጉን ዋንጫ አንድ ጊዜ ያነሳ ሲሆን ቅዱስ ጊዮርጊስ 16 ጊዜ በማሸነፍ የበላይነቱን ይዟል።

ሁለቱ ክለቦች በዘንድሮው የውድድር ዓመት በመጀመሪያ ሳምንት ባደረጉት ጨዋታ ቅዱስ ጊዮርጊስ 1 ለ 0 አሸንፏል። 

የሁለቱ ክለቦች በርካታ ደጋፊዎች ለጨዋታው ድምቀት ይሰጡታል ተብሎ ይጠበቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም