የኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪሚየር ሊግ 22ኛ ሳምንት ዛሬ ይጠናቀቃል - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪሚየር ሊግ 22ኛ ሳምንት ዛሬ ይጠናቀቃል
አዲስ አበባ፤ ሚያዚያ 18 /2018 (ኢዜአ)፦ በኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪሚየር ሊግ የ22ኛ ሳምንት የመጨረሻ ቀን ውሎ ሁለት ጨዋታዎች ይካሄዳሉ።
ከቀኑ ዘጠኝ ሰዓት አዲስ አበባ ከተማ ከቦሌ ክፍለ ከተማ በአበበ ቢቂላ ስታዲየም ይጫወታል።
በሊጉ ካደረጋቸው 21 ጨዋታዎች መካከል ሶስቱን ብቻ ያሸነፈው አዲስ አበባ ከተማ በ16ቱ ሽንፈት አስተናግዷል። በቀሪ ሁለት ጨዋታዎች አቻ ተለያይቷል።
በ21ዱ ጨዋታዎች 14 ግቦችን ከመረብ ላይ ሲያሳርፍ 45 ጎሎች ተቆጥረውበታል። ቡድኑ በ11 ነጥብ 13ተኛ ደረጃን ይዞ ወራጅ ቀጠና ውስጥ ይገኛል።
ተጋጣሚው ቦሌ ክፍለ ከተማ በበኩሉ በሊጉ 21 ጨዋታዎችን አከናውኖ ዘጠኝ ጊዜ ድል ሲቀናው በአምስቱ ተሸንፏል። በቀሪ ሰባት ጨዋታዎች ነጥብ ተጋርቷል። 25 ግቦችን ሲያስቆጥር 19 ጎሎች ተቆጥሮበታል።
ቦሌ ክፍለ ከተማ በ34 ነጥብ ስድስተኛ ደረጃን ይዟል።
በ21ኛ ሳምንት በይርጋጨፌ ቡና የ4 ለ 2 ሽንፈት ያስተናገደው አዲስ አበባ ከተማ ማሸነፍ ላለመውረድ በሚያደርገው ትግል ወሳኝ ሶስት ነጥብ ያስገኝለታል።
ቦሌ ክፍለ ከተማ ካሸነፈ ተከታታይ ድሉን ያስመዘግባል።
በሌላኛው መርሐ ግብር ይርጋጨፌ ቡና ከድሬዳዋ ከተማ ከቀኑ ሰባት ሰዓት በአበበ ቢቂላ ስታዲየም ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።
ይርጋጨፌ ቡና እስከ አሁን በሊጉ ማሸነፍ የቻለው ጨዋታ ብዛት ሶስት ብቻ ነው። 13 ጊዜ ሲሸነፍ አምስት ጊዜ አቻ ወጥቷል። 13 ግቦችን ሲያስቆጥር 33 ጎሎችን አስተናግዷል። ቡድኑ በ14 ነጥብ 12ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል።
ተጋጣሚው ድሬዳዋ ከተማ በበኩሉ 21 ጨዋታዎችን አድርጎ ሰባት ጊዜ ሲያሸንፍ 11 ጊዜ ተሸንፏል። በሶስት ጨዋታዎች ነጥብ ጥሏል። 19 ግቦችን ከመረብ ላይ ሲያሳርፍ 31 ጎሎች ተቆጥረውበታል።
ድሬዳዋ ከተማ በ24 ነጥብ ስምንተኛ ደረጃን ይዟል።
ይርጋጨፌ ቡና ካሸነፈ ተከታታይ ድሉን የሚያስመዘግብ ሲሆን ከወራጅ ቀጠና በመጠኑም ቢሆን እንዲርቅ ያደርገዋል።
በ21ኛ ሳምንት አርባምንጭ ከተማን 1 ለ 0 ያሸነፈው ድሬዳዋ ከተማ ተከታታይ ድሉን ለማስመዝገብ ይጫወታል።