ኢትዮጵያውያን አትሌቶች በለንደን ማራቶን ይጠበቃሉ - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያውያን አትሌቶች በለንደን ማራቶን ይጠበቃሉ
አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 18/2018(ኢዜአ)፦ 46ኛው የለንደን ማራቶን ዛሬ ይካሄዳል።
የኢትዮጵያ አትሌቶች በሁለቱም ፆታዎች ድልን ለመቀዳጀት ከዓለማችን ምርጥ አትሌቶች ጋር ብርቱ ፉክክር ያደርጋሉ።
በሴቶች የወቅቱ የለንደን ማራቶን አሸናፊ ትዕግስት አሰፋ ትጠበቃለች።
አትሌት ትዕግስት በ2025 በተካሄደው የለንደን ማራቶን 2 ሰዓት ከ15 ደቂቃ ከ50 ሴኮንድ የሴቶች ብቻ (Women-only) የዓለም ክብረ ወሰንን ሰብራለች።
አትሌቷ ለውድድሩ አስፈላጊውን ዝግጅት ማድረጓንና በራሷ የያዘችውን ክብረ ወሰን ለመስበር እንደምትሮጥ ገልጻለች።
ትዕግስት ክብሯን ለማስጠበቅ ጠንካራ ፉክክር ታደርጋለች።
ኬንያውያኑ አትሌቶች ሄለን ኦቢሪ እና ጆይስሊን ጄፕኮስኬይ በውድድሩ ላይ ይጠበቃሉ።
በለንደን ማራቶን ይሳተፋሉ ተብለው ሲጠበቁ የነበሩት ኔዘርላንዳዊቷ ሲፋን ሀሰን እና ኬንያዊቷ ፔሬስ ጄፕቺርቺር በጉዳት ምክንያት ከውድድሩ ውጪ ሆነዋል።
ባለምላይ ሹመት፣ መገርቱ ዓለሙ እና ደጊቱ አዝመራው በውድድሩ ላይ ከሚሳተፉ ኢትዮጵያውያን ሴት አትሌቶች መካከል ይጠቀሳሉ።
በወንዶች አትሌት ታምራት ቶላ ለመጀመሪያ ጊዜ በውድድሩ ላይ ይሳተፋል።
አትሌት ታምራት በፓሪስ በተካሄደው 33ኛው የኦሊምፒክ ጨዋታዎች በማራቶን የወረቅ ሜዳሊያ አግኝቷል።
በማራቶን የዓለማችን ዘጠነኛ ፈጣን ሰዓት ያለው ደረሳ ገለታም በውድድሩ ላይ የሚጠበቅ አትሌት ነው።
ዮሚፍ ቀጄልቻ እና ሀጎስ ገብረህይወት በውድድሩ ላይ ከሚሳተፉ አትሌቶች መካከል ይገኙበታል።
የወቅቱ የለንደን ማራቶን አሸናፊ ኬንያዊው አትሌት ሰባስቲያን ሳዌ የኢትዮጵያውያን አትሌቶች ጠንካራ ተፎካካሪ ይሆናል ተብሎ ይጠበቃል።
ዩጋንዳውያኑ ጆሹዋ ቼፕቴጋይ እና ጃኮብ ኪፕሊሞ የሚጠበቁ ሌሎች ተፎካካካሪ አትሌቶች ናቸው።
በዓለም ላይ ካሉ ከሚጠቀሱ ታላላቅ ማራቶኖች አንዱ የሆነው የለንደን ማራቶን፣ ዘንድሮ ከ59 ሺህ በላይ ተሳታፊዎች እንደሚካፈሉበት ተገልጿል።
በሁለቱም ጾታዎች የሚያሸንፉ አትሌቶች በተመሳሳይ የ55 ሺህ የአሜሪካን ዶላር ሽልማት ያገኛሉ።
በተጨማሪም በወንዶች ከ2 ሰዓት 2 ደቂቃ በታች፣ በሴቶች ከ2 ሰዓት ከ15 ደቂቃ በታች የሚገቡ አትሌቶች የ150 ሺህ የአሜሪካን ዶላር የጉርሻ ሽልማት ይበረከትላቸዋል።
ለአትሌቶች በአጠቃላይ ከ1 ነጥብ 2 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር በላይ ሽልማት ተዘጋጅቷል።
እ.አ.አ በ1981 የተጀመረው የለንደን ማራቶን በዓለም አትሌቲክስ የፕላቲኒየም ደረጃ የተሰጠው ውድድር ሲሆን ይህም በጎዳና ላይ ሩጫ ትልቁ የሚባለው ነው።