ኢትዮጵያ እምቅ የታዳሽ ኃይል ሀብቷን ወደ ተጨባጭ የኢኮኖሚ ጥቅም የመለወጥ ስራዋን አጠናክራለች - ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ እምቅ የታዳሽ ኃይል ሀብቷን ወደ ተጨባጭ የኢኮኖሚ ጥቅም የመለወጥ ስራዋን አጠናክራለች - ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)
አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 17/2018 (ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ ያላትን እምቅ የታዳሽ ኃይል ሀብት ወደ ተጨባጭ የኢኮኖሚ ፋይዳ ለመለወጥ የምታደርገው ጥረት በልዩ ትኩረት እየተከናወነ መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገለጹ።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) እና ቀዳማዊት እመቤት ዝናሽ ታያቸው ዛሬ በሐዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክ ተገኝተው፤ የቶዮ ሶላር ኢነርጂ ሁለተኛ ምዕራፍን፣ የኦሪጂን እና የሉሚንቴክ የሶላር ፋብሪካዎችን እንዲሁም የኤች.ዜድ ጋዝ ማምረቻ ፋብሪካን በይፋ መርቀው ከፍተዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በምረቃው ሥነ-ሥርዓት ላይ ባደረጉት ንግግር፤ ኢትዮጵያ የሚገጥሟትን ፈተናዎች ወደ መልካም አጋጣሚ በመቀየር ስኬታማ ተግባራትን እያከናወነች እንደምትገኝ ገልጸዋል።
በተለይም ኢትዮጵያ ከአፍሪካ የእድገትና ዕድል ድንጋጌ (አጎዋ) መውጣቷ ያስከተለውን ክፍተት፣ እንደ አዲስ የኢኮኖሚ ዕድልና መልካም አጋጣሚ መጠቀም መቻሉን ጠቅላይ ሚኒስትሩ አንስተዋል።
ቀደም ሲል የሐዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክ በጨርቃ ጨርቅ ዘርፍ ላይ ብቻ ተገድቦ የነበረ በመሆኑ፣ ከአጎዋ መውጣታችን የውጭ ገበያ አማራጩን በማጥበብ በፓርኩ ህልውና ላይ አደጋ ደቅኖ እንደነበር አስታውሰዋል።
የኢንዱስትሪ ፓርኩ የገጠመው ስጋት፣ በአንድ የኢኮኖሚ ዘርፍ ላይ ብቻ ተመርኩዞ መጓዝ ዘላቂና አዋጪ አለመሆኑን ትልቅ ትምህርት የሰጠ ክስተት እንደነበርም ገልጸዋል።
ከዚህ ተሞክሮ በመነሳት በሀገሪቱ የኢንዱስትሪ ፖሊሲ ላይ መሠረታዊ ማሻሻያ መደረጉን የጠቀሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ በማሻሻያውም አዳዲስ የኢኮኖሚ ዘርፎች እንዲካተቱ መደረጉን አስረድተዋል።
በፖሊሲ ማሻሻያው መሠረት የቬትናምን የኢንዱስትሪ ሽግግር ተሞክሮ በመቀመር፣ በሐዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክ ውስጥ የከፍተኛ ቴክኖሎጂ ምርቶችና የታዳሽ ኃይል መሠረተ ልማቶች እንዲገነቡ መደረጉን ተናግረዋል።
ይህ እርምጃ የሀገሪቱን የኢነርጂ ዋስትና ለማረጋገጥና የማይበገር ሁለንተናዊ እድገትን ዕውን ለማድረግ የተነደፈውን ስትራቴጂ ለማሳካት የሚያስችል መሆኑንም አብራርተዋል።
ዛሬ በይፋ ተመርቀው ሥራ የጀመሩት ሦስቱ የሶላር ፋብሪካዎች በጋራ በዓመት 11 ነጥብ 3 ጊጋዋት ንጹሕ ኃይል የማመንጨት አቅም ያላቸው ሲሆን፤ ይህም የሀገሪቱን የፀሐይ ብርሃን ሀብት ወደ ተጨባጭ ጥቅም የለወጠ ስኬት መሆኑን ገልጸዋል።
ከዚህ ጋር ተያይዞ የተመረቀው የኤች.ዜድ ጋዝ ፋብሪካ በዓመት 900 ቶን ኦክስጅን፣ 40,000 ቶን ናይትሮጅን እና 7 ቶን ሃይድሮጅን ለገበያ እንደሚያቀርብ ጠቁመው፤ ይህም የፋብሪካዎቹ ዘርፈ-ብዙ ውጤቶች መሆናቸውን ተናግረዋል።
በአሁኑ ወቅት በሐዋሳ፣ በደብረብርሃንና በአዲስ አበባ የተጀመሩት የሶላር ኃይል ምርቶች ተደምረው ኢትዮጵያን በቀጣዩ ዓመት የ20 ነጥብ 3 ጊጋዋት ንጹሕ ኃይል ባለቤት እንደሚያደርጓት ጠቅላይ ሚኒስትሩ አመልክተዋል።
እነዚህ ፋብሪካዎች በዓመት ከአንድ ቢሊየን ዶላር በላይ የውጭ ምንዛሪ ለሀገር በማስገኘት የኢኮኖሚ አቅምን በእጅጉ ያጠናክራሉ ብለዋል።
በተጨማሪም ፋብሪካዎቹ አርቴፊሻል ኢንተለጀንስን (AI)፣ ሮቦቲክስንና ዘመናዊ ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም የምርት ሂደታቸውን እያከናወኑ መሆኑን አብራርተዋል።
በመጨረሻም ቴክኖሎጂን በአግባቡ በመተግበር፣ አትራፊና ስኬታማ በሆኑ የኢንዱስትሪ መስኮች ውስጥ ተወዳዳሪ መሆን እንደሚቻል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ገልጸዋል።