መንግስት ለወጣት የዲጂታል ሥራ ፈጣሪዎች ምቹ ሁኔታ ከመፍጠር ባለፈ አስፈላጊውን ድጋፍ እያደረገ ነው - ኢዜአ አማርኛ
መንግስት ለወጣት የዲጂታል ሥራ ፈጣሪዎች ምቹ ሁኔታ ከመፍጠር ባለፈ አስፈላጊውን ድጋፍ እያደረገ ነው
አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 17/2018 (ኢዜአ)፦የኢትዮጵያ መንግስት ለወጣት የፊንቴክ ስታርትአፖች ምቹ ሁኔታን ከመፍጠር ባለፈ አስፈላጊውን ድጋፍ እያደረገ መሆኑን የሥራና ክህሎት ሚኒስትር ዴኤታ ሰለሞን ሶካ ገለጹ።
የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር ከኢንተርፕሪነርሽፕ ልማት ኢንስቲትዩት (EDI) እና ከተባበሩት መንግሥታት ካፒታል ልማት ፈንድ (UNCDF) ጋር በመተባበር፣ ላቅ ያለ የፈጠራ ሥራ ላሳዩ ስምንት የፊንቴክ (FinTech) ስታርትአፖች የገንዘብ ሽልማት መርሀ ግብር አካሂዷል።
የሥራና ክህሎት ሚኒስትር ዴኤታ ሰለሞን ሶካ በሥነ-ሥርዓቱ ላይ እንደገለጹት፤ መንግሥት ለወጣት የዲጂታል ሥራ ፈጣሪዎች ምቹ ሁኔታን ከመፍጠር ባለፈ ተገቢውን ድጋፍ እያደረገ ይገኛል።
መርሐ ግብሩ በኢትዮጵያ የዲጂታል ፋይናንስ ዘርፍን ለማዘመንና የወጣቶችን የፈጠራ አቅም ለማበረታታት ያለመ መሆኑን ጠቁመዋል።
የፊንቴክ መፍትሔዎች ለግብርና፣ ለቱሪዝም፣ ለኢንዱስትሪና ለጠቅላላው የዲጂታል ኢኮኖሚ ግንባታ ያላቸው ፋይዳ የላቀ መሆኑን አጽንኦት ሰጥተዋል።
ለዚህም በዲጂታል 2025 ስትራቴጂ እንደ ቴሌ ብር እና ሲቢኢ ብር ያሉ ውጤቶች ለበርካታ ዜጎች የፋይናንስ ተደራሽነትን ማሳደጋቸውን በአብነት ጠቅሰዋል።
የዘርፉን ተደራሽነት ለማስፋት ወጣቶች የሚፈጥሯቸው ዲጂታል መፍትሔዎች ለዲጂታል ሽግግር ወሳኝ ሚና እንዳላቸው አስገንዝበዋል።
ከ300 በላይ የፊንቴክ ስታርትአፖች መካከል 33ቱ ተለይተው ለፉክክር መቅረባቸውን የገለጹት ሚኒስትር ዴኤታው፤ በዛሬው ዕለት ስምንት ምርጥ ስራ ፈጣሪዎች አሸናፊ በመሆን ከአጋር ድርጅቶች የተገኘውን የ20 ሚሊዮን ብር ሽልማት አግኝተዋል ብለዋል።
አሸናፊዎቹ የተሰጣቸውን የገንዘብ ድጋፍ የንግድ ሞዴሎቻቸውን በተጨባጭ የገበያ ሁኔታ ለመፈተሽና ለማሳደግ እንዲጠቀሙበት ጥሪ አቅርበዋል።
ከተሸላሚዎቹ መካከል የአበዳሪ መተግበሪያ ፈጣሪ ፌቨን ሽመልስ እና የኡጆ መተግበሪያ ፈጣሪ አቤኔዘር እንግዳ፣ መንግሥት ለዘርፉ የሰጠውን ትኩረት አድንቀዋል።
ከተሸላሚዎቹ መካከል የ"አበዳሪ" መተግበሪያ ፈጣሪ ፌቨን ሽመልስ በበኩሏ፤ የብድር አቅርቦትና አሰባሰብን የሚያቀላጥፍ ቴክኖሎጂ በማበልጸግ ለዘርፉ መፍትሄ ማቅረቧን ገልጻለች።
በተመሳሳይ የ"ኡጆ" መተግበሪያ ፈጣሪ አበኔዘር እንግዳ፣ ባህላዊውን የዕቁብ ሥርዓት በቴክኖሎጂ ለማዘመን ለጀመረው ሥራ መንግሥት የሰጠውን ትኩረትና ድጋፍ አድንቋል።
ሽልማቱ ለጀመሩት የፈጠራ ሥራ መነሻ ካፒታል ከመሆኑ ባለፈ፤ ለሌሎች ወጣቶችም ትልቅ መነሳሳትን እንደሚፈጥር ገልጸዋል።