የምርጫ ፍትሐዊነትን ለማረጋገጥ የተቀናጀ የተቋማት ሚና ወሳኝ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የምርጫ ፍትሐዊነትን ለማረጋገጥ የተቀናጀ የተቋማት ሚና ወሳኝ ነው
አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 17/2018 (ኢዜአ)፦የምርጫ ፍትሐዊነትን ለማረጋገጥ የተቀናጀ የተቋማት ሚና ወሳኝ መሆኑን የፌዴራል ሕግና ፍትህ ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር አምባሳደር ደግፌ ቡላ ገለጹ።
የፌዴራል ሕግና ፍትሕ ኢንስቲትዩት "የምርጫ ፍትህ በኢትዮጵያ የዳኝነት፣ የፍትሕና የአስተዳደር አካላት ሚና" በሚል መሪ ሃሳብ የምርምር ኮንፈረንስ አካሂዷል።
በዚሁ ወቅት የኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር አምባሳደር ደግፌ ቡላ፤ የሕግ ሙያተኞችንና የህብረተሰቡን ግንዛቤ የሚያሳድጉ የአውደ ጥናት መድረኮች በየጊዜው እንደሚዘጋጁ ገልጸዋል።
የሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ የዳኝነትና የአስተዳደር አካላት የምክክር መድረክም ሂደቱን ፍትሐዊና ሰላማዊ ለማድረግ ተጨማሪ አቅም መሆኑን ተናግረዋል።
የምርጫ ዴሞክራሲያዊነትን ለማስጠበቅም የፖሊስ፣ ዓቃቤ ሕግና የፍትሕ ተቋማት ተመጋጋቢ የትብብር ሚና እንዳላቸው አስረድተዋል።
የዜጎች የድምፅ መስጫ ወረቀት ቅቡልነት ያለው መንግስት መመስረቻ ሕጋዊ ኃይል መሆኑን አንስተዋል።
የኢትዮጵያን ጠቅላላ ምርጫ ነጻ፣ ፍትሐዊና ቅቡልነት ለማረጋገጥም ህብረተሰቡ፣ የፍትሕና የአስተዳደር ተቋማት ገንቢ ሚናቸውን ሊወጡ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የሥራ አመራር አባል አቶ ተክሊት ይመስል፤ በሕገ-መንግስቱና በአዋጅ በተሰጡ ተግባርና ኃላፊነቶች መሠረት የምርጫ ሂደቱ በገለልተኝነት እየተመራ ነው ብለዋል።
ሰባተኛውን ጠቅላላ ምርጫ በስኬት ለመቋጨትም የሕግና የፍትሕ ተቋማት፣ ተፎካካሪ ፓርቲዎች፣ ዜጎችና ባለድርሻ አካላት ገንቢ ሚናቸውን ሊወጡ እንደሚገባ ጥሪ አቅርበዋል።
ከኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ጠቅላይ መምሪያ የኦፕሬሽን ዋና መምሪያ ሃላፊ አቶ ሙሊሳ አብዲሳ በበኩላቸው ፤ ፖሊስ በሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ የህዝብን ተሳትፎ በማጎልበት የምርጫ ሂደት ሰላማዊነትን የማስጠበቅ ሥራ በብቃት እንደሚወጣ አረጋግጠዋል።
ለዚህም የምርጫ ቁሳቁስ ደኅንነትን የማስጠበቅና የማረጋገጥ ኃላፊነቱን ለመወጣት ከህዝብ ጋር ተከታታይ ውይይቶች እንደሚካሄዱ አስረድተዋል።
ከፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት አቶ ምትኩ ማዳ ባቀረቡት ፅሁፍ፤ የምርጫ ሂደት ፍትሐዊነትን ለማረጋገጥ ለሕግና ሕገ-መንግስታዊ መርህ ተከባሪነት በትኩረት ይሰራል ብለዋል።
ለዚህም በምርጫ ሂደት ተዋናዮች ዘንድ ሊቀርቡ የሚችሉ የሕግና ይግባኝ አቤቱታዎችን አፋጣኝ መፍትሔ መስጠት የሚያስችል ዝግጅት መደረጉን አረጋግጠዋል።
በፍትሕ ሚኒስቴር ከፍተኛ ዐቃቤ ሕግ ጠገነኝ ትርፌ ባቀረቡት ጽሁፍ፤ ማንኛውም አካል ሕገ-መንግሥቱን የማስከበርና ለሕገ-መንግሥቱ ተገዢ የመሆን ኃላፊነት አለበት ብለዋል።
የፍትሕ ሚኒስቴርም ለምርጫ ዓላማ ብቻ ምርመራና ክስ ላይ ለሚሰሩ ዓቃቢያነ ሕግ ስልጠና በመስጠት ግብረ ኃይልና ቡድኖችን በማዋቀር ወደሥራ ማስገባቱን አስረድተዋል።