ቀጥታ፡

ባሳለፍነው ሳምንት …

ከሚያዝያ 11 እስከ ሚያዝያ 17 ቀን 2018 . ከተከናወኑ ዐበይት ጉዳዮች መካከል

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (/) ከተለያዩ ሀገራት እና ዓለም አቀፍ ተቋማት የሥራ ኃላፊዎች ጋር መምከራቸው

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (/) ከደቡብ ሱዳን ፕሬዚዳንት ሳልቫ ኪር ማያርዲት ጋር ተወያይተዋል።

በዚሁ ወቅትም፤ ቀጣናችንን መልክ በሚያሲዙ እና የጋራ መፃኢ የልማት ጉዳዮች ላይ የሁለትዮሽ ውይይት አድርገናል ብለዋል።

በሁለቱ  ሀገሮች በላቀ እድገትና ተጠቃሚነት ዙሪያ መረጃ የተለዋወጥን ሲሆን፤ የኢኮኖሚ ትስስርን በጠንካራ ትብብር እና በኢንቨስትመንት በመደገፍ እድሎችን የምናሰፋባቸውን የቀጣይ ስራዎች የተመለከተ ፍሬያማ ምክክር አድርገናል ሲሉም ገልፀዋል።

ባሳለፍነው ሳምንት ከተከናወኑ ዐበይት ጉዳዮች አንዱ፤ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (/) ከአውሮፓ ኅብረት የዓለም አቀፍ ትብብር ኮሚሽነር ጆሴፍ ሲከላ ጋር መምከራቸው ነው። በዚሁ ወቅትም፤ ከአውሮፓ ኅብረት ጋር ስላለን የረጅም ጊዜ ትብብር መክረናል ብለዋል።

በተመሳሳይም ከፕሬዚዳንት ኡመር ጌሌህ የተላከ መልዕክት ይዘው ከመጡት የጂቡቲ የውጭ ጉዳይ እና ዓለም አቀፍ ትብብር ሚኒስትር አብዱልቃድር ሁሴን ኦማር ጋር ተወያይተዋል። በዚሁ ወቅትም በሀገሮቻችን መካከል ስላለው ትብብር ተወያይተናል ብለዋል ጠቅላይ ሚኒስትሩ።

እንዲሁም የአፍሪካ በሽታ መቆጣጠሪያ እና መከላከያ ማዕከል (Africa CDC) ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ዣን ካሴያ ጋር ውጤታማ ውይይት አድርገዋል። በዚሁ ወቅትም፤ በአፍሪካ ሕብረት የሰው ሠራሽ አስተውሎት (AI) እና የዲጂታል ጤና ዘርፍ መሪ (Champion) በመሆን የተሰጠኝን አዲስ ኃላፊነት በሚመለከት በስፋት ተነጋግረናል ብለዋል።

በጤናው ዘርፍ የሚገጥመንን ተለዋዋጭ ተግዳሮቶች ለመወጣት የሰው ሠራሽ አስተውሎትንና የዲጂታል ቴክኖሎጂዎችን ዐቅም መጠቀም የጤና ሥርዓታችንን ለማጠናከር፣ ተደራሽነትን ለማስፋፋት እና ለሕዝባችን የተሻለ ውጤት ለማስመዝገብ ወሳኝ ነው ብለዋል። ኢትዮጵያ ያላትን ልምድ ለአህጉሩ ለማካፈል እንዲሁም በፍጥነት ከሚለዋወጠው የቴክኖሎጂው ዓለም ጋር ውጤታማ በሆነ መልኩ ለመራመድ የሚያስችሉ ጠንካራ አጋርነቶችን ለመመሥረት ያላትን ቁርጠኝነት ዳግም ታረጋግጣለች ሲሉም አስታውቀዋል።

በኢትዮጵያ የበቆሎ መስኖ ውጤታማነት

ባሳለፍነው ሳምንት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (/) ትኩረት ሰጥተን እየሠራንባቸው ከሚገኙት ምርቶች አንዱ የሆነው የበቆሎ መስኖ ሥራ፤ ከፍ ባለ ስኬት ላይ ይገኛል ማለታቸው ይታወሳል። የተገኘው ጅምር ውጤትም፤ ኢትዮጵያ የምግብ ዕርዳታ ከመቀበል ወጥታ ራሷን መመገብ የምትችል ሀገር የማድረግ ታላቁ ህልማችን ዕውን የሚሆንበት መንገድ ላይ ስለመሆኑ አመላካች ነው ብለዋል።

መሶብ የሞባይል አገልግሎት መመረቅ

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (/) ባሳለፍነው ሳምንት፤ ካቀድናቸው አምስት የልማት ምሰሶዎች መካከል ቴክኖሎጂን ለአገልግሎት ዘርፉ እንደ ዋነኛ መሣሪያ በመጠቀም፣ የአገልግሎት ቅልጥፍናንና ተደራሽነትን ለማሻሻል በቁርጠኝነት እየሠራን ነው ሲሉ መልዕክት አስተላልፈዋል።

በመሶብ አገልግሎት የታየው ከፍተኛ የደንበኞች እርካታ የስራውን ውጤታማነት ያረጋገጠ መሆኑን የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትሩ የአሰራሩን ይበልጥ መስፋፋት አስፈላጊነትም ገልጸዋል።ዜጎች ጊዜያቸውን በአግባቡ እንዲጠቀሙ የተቀናጁ አገልግሎቶችን ተደራሽ የማድረጉ ስራ ተጠናክሮ አንደሚቀጥልም ጠቁመዋል።

በተመሳሳይ በዚሁ ጉዳይ ላይ የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ባጋራው መረጃ ዛሬ ሥራ የጀመረው የመሶብ ተንቀሳቃሽ አውቶቡስ አገልግሎት፤ አስፈላጊ የሆኑ የመንግሥት አገልግሎቶችን በቀጥታ ወደ ማኅበረሰቡ ለማድረስ የተወሰደ ትልቅ እርምጃ ነው ብሏል። ለአገልግሎት የተደራጀው አውቶቡስ ሙሉ ቁሳቁስ የተሟላለትና ራሱን የቻለ የአገልግሎት ማዕከል ሆኖ የተዘጋጀ ሲሆን፤ ቀልጣፋና አስተማማኝ አሠራርን ለማረጋገጥ ዘመናዊ ቴክኖሎጂዎችንና ሥርዓቶችን አቀናጅቶ የያዘ መሆኑን ገልጿል።

አውቶቡሱ የአገልግሎት ፍሰቱን የሚያደራጅ የሰልፍ ማስተናገጃ ሥርዓት እንዳለውና የተለያዩ የክፍያ አማራጮች ማካተቱንም አመላክቷል። ለአገልግሎቱ የሚያስፈልገውን ኃይል በከፊል 8 ኪሎ ዋት የፀሐይ ብርሃን የሚያገኝ ሲሆን፤ አስተማማኝ ኢንተርኔትም ተገጥሞለታል።

በተጨማሪም የአገልግሎት አሰጣጡን ደኅንነትና ግልፅነትን ለመከታተል ካሜራዎች ተገጥመውለታል፤ መፍትሔ አምጪ ሆኖ የተዘጋጀው የፈጠራ ውጤትና ተንቀሳቃሽ ክፍል፤ ከስምንት የተለያዩ የመንግሥት ተቋማት የሚገኙ የሚከተሉትን ወሳኝ አገልግሎቶች ይሰጣል፦

አዲስ የግብር ከፋይ መለያ ቁጥር (TIN) መስጠት፣ የንግድ ፈቃድ ማውጣትና ማደስ፣  ለመንጃ ፈቃድ የሚያስፈልግ የሕክምና ምርመራ ማድረግ፣ የነዋሪነት መታወቂያ ማደስና የልደት ምዝገባ፣ የመንጃ ፈቃድ መስጠትና የተሽከርካሪ ታርጋ ማደስ፣ የኢትዮጵያ ፖስታ አገልግሎት የመንገድ ፈንድ ክፍያን ማከናወን፣ የብሔራዊ መታወቂያ ምዝገባና የመረጃ እርማት፣ በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት በኩል የሚሰጥ የቅድመ ክፍያ የኤሌክትሪክ አገልግሎቶችን ይሰጣል።

በአጠቃላይ ይህ ተንቀሳቃሽ አውቶቡስ የስምንት ተቋማትን አገልግሎት በአንድ ላይ በማቀናጀት፣ ዜጎች ረጅም ርቀት ሳይጓዙ ወይም የተለያዩ ቢሮዎችን ማንኳኳት ሳያስፈልጋቸው ምቹ፣ ቀልጣፋና ተደራሽ የሆነ መፍትሔ ይሰጣል።

100 ቀናትና 9 ወራት የመንግሥት ሥራ አፈጻጸም ግምገማ

ባሳለፍነው ሳምንት የሥራ ዘመኑ 3 100 ቀናት የመንግሥት ሥራ አፈፃፀም ከዘጠኝ ወራት አጠቃላይ አፈፃፀም ጎን ለጎን መገምገሙን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (/) ገልጸዋል። በዚሁ ወቅትም፤ የቀየስነው አዲሱ የኢኮኖሚ አካሄድ በአጭር ጊዜ ትግበራ ጠንካራ ባለሁለት አሃዝ የዕድገት ሂደትን አስመዝግቧል ብለዋል። ጥረቶቻችን የበለጠ ጽኑ፣ ተወዳዳሪ እና አካታች ኢኮኖሚ ለመገንባት ያለንን አቋም እና የመተግበር ዐቅም ያሳያሉ ሲሉም አስገንዝበዋል።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ስለ 3ኛው 100 ቀን አፈጻጸም

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ በተገኙበት፤ 2018 በጀት ዓመት 3ኛው 100 ቀን አፈጻጸም ሪፖርት ከፌደራል ተቋማት አመራሮች ጋር ተገምግሟል። በዚሁ ወቅትም አቶ ተመስገን፤ ኢትዮጵያ ትልቅ ሀገር ናት፤ የሚገባትም ትልቅ ሥፍራ ነው፤ እኛ ደግሞ የዚህ ታሪክ ሠሪዎች የመሆን ዕድል በእጃችን ላይ ነው ሲሉ አዝገንዝበዋል።

በኮሪደር ልማት፣ በገበታ ለሀገር ፕሮጀክቶችና በዲጂታል ኢትዮጵያ ዘርፍ የተካሄደው የመሠረተ-ልማት አብዮት የሀገራችንን እንዲሁም የከተሞቻችንን ገጽታና አገልግሎት ቀይሯል ብለዋል።

በስንዴ ልማትና በሌማት ትሩፋት አማካኝነት የተረጅነትን ቀንበር ሰብረን ወደ  ምግብ ሉዓላዊነት እየተጓዝን ነው ያሉት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ በዲፕሎማሲው መስክም ኢትዮጵያ ከእርዳታ ጠባቂነት ወደ ንግድና ኢንቨስትመንት አጋርነት በመሸጋገር፣ በዓለም አቀፍ መድረክ ተደማጭነቷን ወደ ላቀ ምዕራፍ አሳድጋለች ብለዋል።

የሚኒስትሮች ምክር ቤት ውሳኔዎች

ባሳለፍነው ሳምንት የሚኒስትሮች ምክር ቤት ባካሄደው 54 መደበኛ ስብሰባ በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ተወያይቶ ውሳኔዎችን አሳልፏል። በዚህም መሠረት ምክር ቤቱ፤ በሁለት የፋይናንስ ድጋፍና ብድር ስምምነቶች፣ በሀገራችን የዩሪያ ማዳበሪያ ማምረቻና ማቀነባበሪያ ፋብሪካን የሚመለከት የኢንቨስትመንት ማበረታቻና ጥበቃ ስምምነት፣ የቁልፍ መሠረተ-ልማቶች የሳይበር ደኅንነት ረቂቅ አዋጅ፣ በሥድስት ዓለም አቀፍ የሁለትዮሽ ስምምነቶች እንዲሁም የኢትዮጵያ እሳት እና ሌሎች ቅጽበታዊ አደጋዎች አገልግሎት ማቋቋሚያ ደንብ ላይ መክሮ በማጽደቅ ውሳኔዎችን አሳልፏል።

ዓለምን በሚበይነው የዲጂታል ዘርፍ ሪፎርም የተገኙ ቁልፍ ውጤቶች

የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ዓለምን በሚበይነው የዲጂታል ዘርፍ ሪፎርም የተገኙ ቁልፍ ውጤቶች ብሎ ባጋራው መረጃ፤ በመሠረተ-ልማት (5G እና 4G ሽፋን መስፋፋት) በዲጂታል መሳሪያዎች (ስማርት ስልኮችን በሀገር ውስጥ መገጣጠም) በዲጂታል መንግሥት (በመሶብ አንድ ማዕከል አገልግሎት 2 ሺህ 260 አገልግሎቶች በአንድ ቋት መደራጀት፣ ዲጂታል ክፍያዎች፣ የፍትሕ ተደራሽ ስማርት ችሎት እና ዲጂታል ፖሊስ) የሚሉትን አንስቷል።

በተጨማሪም በዲጂታል ክኅሎት (5 ሚሊየን ኮደሮች ስልጠና፣ ትምህርት ቤቶችን በኢንተርኔት (SchoolNet) በሦስተኛ ዲግሪ (PhD) ደረጃ የሰው ሠራሽ አስተውሎት (AI) ምርምር እና ስታርት አፖችን በዕውቀትና በፈጠራ ማብቃት፣ በተቋማት ግንባታ (ዲጂታል ስታቲስቲክስ እና ልማት አስተዳደር፣ AI ኢንስቲትዩት፣ AI ዩኒቨርሲቲ እና የኢንፎርሜሽን መረብ ደኅንነት አሥተዳደር) በሕግ ማዕቀፍ ተዓማኒነት (በፋይዳ መታወቂያ 40 ነጥብ 9 ሚሊየን በላይ ዜጋ ተካቷል፣ የግል መረጃ ጥበቃ አዋጅ፣ የዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 ስትራቴጂ እና የኤሌክትሮኒክ ፊርማ ተግባራዊነት) የሚሉት ጉዳዮችን ጠቅሷል።

የልማት ዕቅድ ማስፈፀሚያ ኢንሼቲቮችን በመለየት መተግበር

የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ባሳለፍነው ሳምንት ባጋራው መረጃ፤ በአረንጓዴ ዐሻራ የሀገሪቱ የደን ሽፋን 23 ነጥብ 6 በመቶ መድረሱን አስታውቋል።

ሀገራዊ የስንዴ ልማትን በተመለከተም ኢትዮጵያ የምግብ ዋስትናን እና ሉዓላዊነትን እያረጋገጠች ትገኛለች ያለው ጽሕፈት ቤቱ፤ አዳዲስ የግብርና ዕውቀቶች እየተስፋፉ፣ የሀገር ውስጥ ኢንዱስትሪዎች ግብዓቶችን እያገኙ፣ ውድ የሆኑ የውጭ ምርቶች በሀገር ውስጥ እየተተኩ፣ የሥራ ዕድሎች እየሰፉና የአርሶ አደሮች ገቢ እየጨመረ ይገኛል ብሏል።

ከሌማት ትሩፋት አንጻርም፤ የግብርና ግብዓቶች አቅርቦት እና ምርታማነት እየጨመረ ነው፤ የተመጣጠነ ምግብ በቀላሉና በተመጣጣኝ ዋጋ እንዲገኝ ከማድረግ ባለፈ፣ አነስተኛ የንግድ እንቅስቃሴዎች እንዲሳለጡና አካባቢው ይበልጥ እንዲጠበቅ እያደረገ ይገኛል ሲል ገልጿል።

ዲጂታል ኢትዮጵያን አስመልክቶም፤ የሕግ፣ የፋይናንስ እና የማንነት መታወቂያ (ID) ሥርዓቶች ወደ ዲጂታል እየተቀየሩ ነው። የኢንተርኔት ተደራሽነትና የኦንላይን አገልግሎቶች እየተስፋፉ፣ የሞባይል ክፍያ ሥርዓት እየተጠናከረ እንዲሁም የኢ-ኮሜርስ ንግድ የዜጎችን ጊዜና ገንዘብ እያተረፈ ነው ብሏል።

የከተማና የገጠር ኮሪደር ልማትም፤ የከተሞች መሠረተ-ልማት በአረንጓዴ ትራንስፖርት እየዘመነ ነው ያለው ጽሕፈት ቤቱ፤ ይህም የዜጎችን የኑሮ ጥራት እያሻሻለ፣ የአካባቢ ንግድን እያነቃቃ እንዲሁም በከተማና በገጠር መካከል ያለውን ትስስር እያጠናከረ እንደሚገኝ አስታውቋል።

ከኢትዮጵያ ታምርት አኳያም፤ የማምረት ዐቅምና የምርቶች እሴት የመጨመር ሂደት እየተሻሻለ ነው ብሏል። ከውጭ የሚገቡ ምርቶች በሀገር ውስጥ እየተተኩ፣ የውጭ ምንዛሪ ግኝት እያደገ፣ የግብዓት አቅርቦት እየተጠናከረና አዳዲስ የሥራ ዕድሎች እየተፈጠሩ ስለመሆኑም አመላክቷል።

እያንዳንዱ ምሰሶ ፈተናዎችን ወደ መልካም አጋጣሚ በመቀየር፣ ጠንካራ እና ራሷን የቻለች ኢትዮጵያን ለመገንባት ጉልህ ሚና እየተጫወተ ነው ሲልም በአጽንዖት ገልጿል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም