የግብርና ቴክኒክና ሙያ ኮሌጆች የግብርናውን ክፍለ ኢኮኖሚ ለማዘመን ጉልህ ድርሻ እየተወጡ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የግብርና ቴክኒክና ሙያ ኮሌጆች የግብርናውን ክፍለ ኢኮኖሚ ለማዘመን ጉልህ ድርሻ እየተወጡ ነው
ሮቤ፤ ሚያዝያ 17/2018 (ኢዜአ)፦ የግብርና ቴክኒክና ሙያ ኮሌጆች የወጣቶችን የሥራ ፈጣሪነት ክህሎት ከማሳደግ ባሻገር የግብርናውን ክፍለ ኢኮኖሚ ለማዘመን ጉልህ ድርሻ እየተወጡ መሆኑ ተመላከተ።
የአጋርፋ ግብርና ቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ሥልጠና ኮሌጅ በተለያዩ ሙያዎች በደረጃ 4 ያሰለጠናቸውን 592 ተማሪዎችን አስመርቋል።
ተማሪዎቹ በተፈጥሮ ሃብት ጥበቃ፣ በእጽዋት ሳይንስ፣ በእንስሳት ሳይንስ፣ በመሬት አስተዳደርና ልማት ዘርፍ የተመረቁ መሆናቸውም ተመልክቷል።
በምረቃ መርሃ ግብሩ ላይ የተገኙት የመደ ወላቡ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ብርሃነመስቀል ጠና (ዶ/ር) እንዳሉት በለውጡ ዓመታት የክህሎት ልማትንና የቴክኒክና ሙያ ዘርፍን ለማጠናከር በተሰሩ ሥራዎች አበረታች ለውጦች ታይተዋል።
በዚህም ተግባራዊ የተደረጉ ክህሎት መር የፖሊሲ እርምጃዎች ወጣቶች ከስራ ፈላጊነት ወደ ስራ ፈጣሪነት እንዲሸጋገሩ በማድረግ የስራ ፈጣሪነት ባህል እንዲነቃቃ አስችሏል ብለዋል።
በተለይ በግብርናው ዘርፍ ላይ ትኩረት በማድረግ የሚያሰለጥኑ የግብርና ቴክኒክና ሙያ ኮሌጆች የወጣቶችን የሥራ ፈጣሪነት ክህሎት ከማሳደግ ባሻገር የግብርናውን ክፍለ ኢኮኖሚ ለማዘመን ጉልህ ድርሻ እየተወጡ መሆኑን አመልክተዋል።
በተጨማሪም ዘመናዊ የመሬት አስተዳደር ልማትን ተደራሽ በማድረግ በዘርፉ የሚስተዋሉ ተግዳሮቶች እንዲፈቱ ትልቅ አቅም እንደሚፈጥሩም አስረድተዋል።
የአጋርፋ ግብርና ቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ሥልጠና ኮሌጅም የዚሁ አንዱ ማሳያና በዘርፉ የተማረ የሰው ኃይል በማፍራት ረገድ አይነተኛ ሚና እየተወጣ ያለ አንጋፋ ተቋም መሆኑንም አክለዋል።
ተመራቂዎችም በኮሌጁ ቆይታቸው ያገኙትን የንድፈ ሀሳብ ዕውቀት በአካባቢያቸው ከሚገኙ ፀጋዎች ጋር በማቀናጀት በተማሩት ሙያ አርሶና አርብቶ አደሩን በቅንነት እንዲያገለግሉ አስገንዝበዋል።
የአጋርፋ ቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ሥልጠና ኮሌጅ ዲን አቶ ፍራኦል ኢደኦ በበኩላቸው እንደገለጹት፤ ኮሌጁ የግብርና ክፍለ ኢኮኖሚውን ለማዘመን በዘርፉ የተማረ የሰው ኃይል የማፍራት ኃላፊነቱን እየተወጣ ነው።
በተለይ በግብርናው ዘርፍ ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ ረገድ የሚስተዋሉ ተግዳሮቶችን በጥናትና ምርምር እንዲፈቱ ለማስቻል በዘርፉ የተመረቁ ሰልጣኞች ድርሻ ከፍተኛ መሆኑን አክለዋል።
ኮሌጁ ከመማር ማስተማሩ ተግባር በተጓዳኝ የአካባቢውን ማህበረሰብ ተጠቃሚ የሚያደርጉ በርካታ ምርምሮችና የማህበረሰብ አገልግሎቶችን እያከናወነ መሆኑንም ተናግረዋል።
በመሬት አስተዳደርና ልማት ዘርፍ የተመረቀው ፉአድ ሲራጅ፤ በኮሌጁ የትምህርት ቆይታው ያገኘውን ዕውቀት ለማህበረሰብ አገልግሎት ለማዋል ቁርጠኛ መሆኑን ገልጿል።
ተማሪ አቤል አዱኛ በበኩሉ፤ በተለይ በተፈጥሮ ሃብት ልማት ዘርፍ በአገሪቱ የተጀመሩ ውጤታማ ሥራዎች ይበልጥ እንዲጠናከሩ የበኩሌን እወጣለሁ ብሏል።
በምረቃ መርሐግብሩ በትምህርታቸው ብልጫ ላስመዘገቡ ተማሪዎች የሜዳሊያና የዋንጫ ሽልማት በዕለቱ የክብር እንግዶች ተበርክቷል።