ቀጥታ፡

የዋንጫ ተፎካካሪው ኢትዮ ኤሌክትሪክ ወሳኝ ድል ተቀዳጀ

አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 17/2018 (ኢዜአ)፦ በኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪሚየር ሊግ 22ኛ ሳምንት መርሀግብር ኢትዮ ኤሌክትሪክ አርባምንጭ ከተማን 2 ለ 0 አሸንፏል።

በአበበ ቢቂላ ስታዲየም በተካሄደው ጨዋታ ዳግማዊት ሰሎሞን እና ብርሃን ኃይለሥላሴ ግቦቹን አስቆጥረዋል። 

ዳግማዊት ሰሎሞን (ኢትዮ ኤሌክትሪክ) የጨዋታው ኮከብ ሆና ተመርጣለች። 

ኢትዮ ኤሌክትሪክ 18ኛ ድሉን በማስመዝገብ ነጥቡን 57 ቢያደርስም፣ ተመሳሳይ ነጥብ  ባለው ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በግብ ክፍያ ተበልጦ ሁለተኛ ደረጃን ይዟል። 

በሁለቱ ቡድኖች መካከል ያለው የዋንጫ ፉክክር አጓጊነቱ ጨምሯል።


 

በውድድር ዓመቱ 16ኛ ሽንፈቱን ያስተናገደው አርባምንጭ ከተማ በ10 ነጥብ የመጨረሻውን 14ኛ ደረጃን ይዟል።

አርባምንጭ ከተማ ባለፉት 15 የሊግ ጨዋታዎች ከድል ርቋል። በውድድር ዓመቱ ሁለት ጨዋታዎችን ብቻ ያሸነፈው ቡድኑ በሊጉ የመቆየት እድሉ ጠባብ ሆኗል።

የኢትዮ ኤሌክትሪኳ አጥቂ ዳግማዊት ሰሎሞን በሊጉ ያስቆጠረቻቸውን ግቦች ወደ 23 ከፍ በማድረግ የከፍተኛ ግብ አስቆጣሪነቷን አጠናክራለች።

ዛሬ በተደረገ ሌላኛው ጨዋታ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ባህር ዳር ከተማን 3 ለ 0 በመርታት መሪነቱን አጠናክሯል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም