ቀጥታ፡

በክልሉ በግብርናው ዘርፍ የምርት እድገት ለማስመዝገብ በርብርብ መስራት ይገባል- ድረስ ሳህሉ (ዶ/ር)

ባህርዳር ፤ ሚያዝያ 17/2018 (ኢዜአ)፦ በአማራ ክልል በግብርናው ዘርፍ የሚጠበቀውን የምርት እድገት ለማስመዝገብ በየደረጃው ርብርብ ማድረግ እንደሚያስፈልግ በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የገጠር ክላስተር አስተባባሪ ድረስ ሳህሉ (ዶ/ር) ገለጹ።

ቢሮው የ2018/2019 የመኸር ሰብል ልማት የንቅናቄ መድረክ ዛሬ በባህርዳር ከተማ አካሂዷል።


 

የገጠር ክላስተር አስተባባሪው ድረስ ሳህሉ (ዶ/ር) በዚሁ ወቅት እንደገለጹት በመጭው የመኸር ምርት ወቅት የአርሶ አደሩን የምግብ ሉአላዊነትን የሚያረጋግጥና ለገበያ የሚተርፍ ምርት ማምረት ይጠበቃል።

ለዚህም አርሶ አደሩን በልማት ቡድን አደራጅቶ ወደ ሰብል ልማቱ በማስገባትና ከልማዳዊ አሰራር በማላቀቅ በአዳዲስ እሳቤዎች ላይ የተመሰረተ አመራረት ዘይቤን መከተል እንደሚገባ ገልጸዋል።

በየደረጃው ያለው አመራርና ባለሙያም አርሶ አደሩ ዘመኑ የደረሰበትን የማምረት እውቅትን እንዲጨብጥ በማድረግ ስራ ላይ  በማተኮር ለምርት እድገቱ ስኬት በቁርጠኝነት ሊሰራ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

ይህም የግብርና ኤክስቴንሽንን በተሟላ በመተግበር፣ በሜካናይዜሽን ላይ በማተኮር፣ በኩታገጠምና የኮንትራት ፋርሚንግ አሰራርን በማስፈን ከምግብ በዘለለ ለገበያ የሚተርፍ ምርት ለማምረት የሚያስችል መሆኑን ተናግረዋል።

"ያልተደራጀ ባለሙያና አርሶ አደር ምርታማነትን ማረጋገጥ አይችልም" ያሉት ዶክተር ድረስ አርሶ አደሩ በተደረጃ አግባብ በሰብል ልማቱ ላይ እንዲረባረብ ማድረግ ተገቢ ነው ብለዋል።


 

የክልሉ ግብርና ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ቃልኪዳን ሽፈራው በበኩላቸው በመጭው የመኸር ወቅት  በዘር ከሚሸፈነው 5 ነጥብ 5 ሚሊዮን ሄክታር መሬት ውስጥ 70 በመቶውን በገበያ ተፈላጊ የሆኑ ሰብሎች ለመሸፈን እየተሰራ ነው።

ምርታማነትን ለማሳደግም ግብዓትና ቴክኖሎጂን በአግባቡ ከመጠቀም ባሻገር የተጠናከረ የአረምና የተባይ ቁጥጥር ስራን ለማከናወን አቅጣጫ ተቀምጦ ከወዲሁ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

በክልል ደረጃ የተጀመረውን የንቅናቄ መድረክ በቀጣይ እስከ ታች ድረስ ለሚገኘው ባለሙያና አርሶ አደር በማውረድ መግባባት ይፈጠራል ብለዋል፡፡

በንቅናቄ መድረኩ ላይ ከክልልና ከምዕራብ አማራ ከሚገኙ ዞኖች የተውጣጡ የግብርና አመራሮችና ባለድርሻ አካላት ተሳትፈዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም