የኢትዮጵያን የስፖርት ሃብቶች አዕምሯዊ መብት ባለቤትነት በማረጋገጥ ለገፅታ ግንባታና ለኢኮኖሚ ዕድገት መጠቀም ያስፈልጋል - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያን የስፖርት ሃብቶች አዕምሯዊ መብት ባለቤትነት በማረጋገጥ ለገፅታ ግንባታና ለኢኮኖሚ ዕድገት መጠቀም ያስፈልጋል
አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 17/2018(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያን የስፖርት ዘርፍ ሃብቶች አዕምሯዊ መብት ጥበቃ ባለቤትነት በማረጋገጥ ለገፅታ ግንባታና ለኢኮኖሚ ዕድገት መጠቀም እንደሚያስፈልግ የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚንስቴር ገለጸ።
የዓለም አዕምሯዊ ንብረት ቀን ''አዕምሯዊ ንብረትና ስፖርት፡ እንዘጋጅ፣ እንጀምር፣ እንፍጠር” በሚል መሪ ሃሳብ በተለያዩ ሁነቶች በአዲስ አበባ ተከብሯል።
በዝግጅቱ በስፖርት ዘርፍ የሚጠበቁ የአዕምሯዊ ንብረት መብቶችን ለህዝብ ዕይታ በማቅረብ የፈጠራና ስፖርት ሃብቶችን ጥቅም ላይ ማዋል በሚያስችሉ አጀንዳዎች ላይ የምክክር መድረክ ተካሂዷል።
በሚኒስትር ዴኤታ ማዕረግ የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር አማካሪ ፎዚያ አሚን(ዶ/ር)፤ በስፖርት ዘርፍ የኢትዮጵያን ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪነት የሚያሳድጉ መሠረተ ልማቶች እየተገነቡ ነው ብለዋል።
የስፖርት ሁነቶች ከውድድር መድረክነት ባሻገር ከሀገር ስምና ዝና፣ ፋሽን፣ ዲዛይንና ከመገናኛ ብዙኅን ስርጭት ጋር የተቆራኙ መሆናቸውን ተናግረዋል።
በዚህም የስፖርት ተወዳዳሪዎች የግልና የጋራ ፈጠራ፣ ንድፍና የመልካም ዝና ታሪኮችን በአግባቡ ጥቅም ላይ ለማዋል የአዕምሯዊ ንብረት ጥበቃ ማድረግ እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል።
ባለድርሻ አካላትም የስፖርት ሃብቶችን አዕምሯዊ ንብረት ጥበቃ በማረጋገጥ ለሀገር ገፅታ፣ ለኢኮኖሚ ዕድገትና ለዘርፉ ተዋናዮች ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ገንቢ ሚና ሊወጡ ይገባል ብለዋል።
የኢትዮጵያን ምርትና አገልግሎቶች በዓለም ንግድ ሥርዓት ለማሳለፍ በሚደረገው ሰፊ ዝግጅትም የስፖርት ዘርፍ አዕምሯዊ ንብረት ጥበቃ ሥርዓትን ማጠናከር እንደሚያስፈልግ አጽንኦት ሰጥተዋል።
የኢትዮጵያ አዕምሯዊ ንብረት ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ወልዱ ይመስል በበኩላቸው፤ የስፖርት ዘርፍ አዕምሯዊ ንብረት ጥበቃ የአትሌቶችን ዓለምአቀፍ ዕውቅና ለማላቅ ከፍተኛ ሚና አለው ብለዋል።
ለዚህም የኢትዮጵያን ስምና ዝና በዓለም መድረክ ያስጠሩ አትሌቶችን የግልና የጋራ ድል አዕምሯዊ መብት ጥበቃ እንዲደረግላቸው ለማስቻል እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።
የዓለም አዕምሯዊ ንብረት ቀንም የባለድርሻ አካላትን ግንዛቤ በማሳደግ የስፖርት ሃብቶችን አዕምሯዊ ንብረት ባለቤትነት ጥበቃ ለማረጋገጥ እንደሚረዳ ተናግረዋል።
የኢትዮጵያን የስፖርት ዘርፍ ሃብቶችን አዕምሯዊ መብት ጥበቃ ማረጋገጥ ያስፈልጋል ያሉት ደግሞ በኢትዮ-አሊያንስ አድቮኬሲ የአእምሯዊ ንብረትና ዓለምአቀፍ ግንኙነት ዋና ዳይሬክተር ትዕግስት ደሱ (ዶ/ር) ናቸው።
የስፖርት ቤተሰቡም የአትሌቲክስና የተለያዩ የስፖርት ዘርፍ ሃብቶችን ሕጋዊ ዕውቅና በማስገኘት የአዕምሯዊ መብት ጥበቃ ምዝገባ ማደረግ እንደሚኖርበት አስገንዝበዋል።