ቀጥታ፡

በሀገር አቀፍ ደረጃ ወባን ለመከላከልና ለመቆጣጠር በተሰሩ ስራዎች ስርጭቱን በከፍተኛ ሁኔታ መቀነስ ተችሏል

ድሬዳዋ፤ ሚያዝያ 17/2018(ኢዜአ)፦ የወባ በሽታን ለመከላከል እና ለመቆጣጠር በተከናወኑ የተለያዩ ተግባራት ስርጭቱን በከፍተኛ ሁኔታ መቀነስ እንደተቻለ ጤና ሚኒስቴር ገለጸ።

የድሬዳዋ አስተዳደር ከንቲባ ከድር ጁሃር በበኩላቸው በአስተዳደሩ ወባን ለመከላከል በተሰሩ ስራዎች የተገኙ ውጤቶችን ቀጣይነት ለማረጋገጥ በቁርጠኝነት እየተሰራ ነው ብለዋል።

አለም አቀፍ የወባ ቀን "ወባን ለማጥፋት እንነሳ፤ አሁንም እንችላለን" በሚል መሪ ሃሳብ  በተለያዩ ዝግጅቶች ዛሬ በድሬዳዋ ተከብሯል።

በስነ-ስርዓቱ የተገኙት በጤና ሚኒስቴር የበሽታዎች መከላከልና መቆጣጠር መሪ ስራ አስፈፃሚ ዶክተር ህይወት ሰለሞን እንደገለፁት፤ በሀገር አቀፍ ደረጃ ወባን ለመከላከልና ለመቆጣጠር በተሰሩ ስራዎች ስርጭቱን በከፍተኛ ሁኔታ መቀነስ ተችሏል።



የወባ በሽታን ለመከላከልና ለመቆጣጠር በ560 ወረዳዎች እና በ12 ሺህ 260 ቀበሌዎች በተከናወኑ ሰፊ እና የተቀናጁ ተግባራት ተጨባጭ ለውጦች መመዝገባቸውን አንስተዋል።

ለወባ በሽታ መንስኤ የሆኑ የትንኝ መራቢያ ስፍራዎችን በማፋሰስና በማድረቅ፣ ከ16 ሚሊየን በላይ ዘመናዊ አጎበሮችን ለተጋላጭ የህብረተሰብ ክፍሎች በማሰራጨት ከ32 ሚሊየን በላይ ነዋሪዎችን ጤና መጠበቅ መቻሉን ገልፀዋል።

በተጨማሪም ከ2 ሚሊየን በላይ ተጋላጭ ቤቶች ፀረ-ትንኝ ኬሚካል ርጭት በማካሄድ የተሰሩ ስራዎች የወባ ስርጭትን 46 በመቶ መቀነስ አስችለዋል ብለዋል።

የስርጭቱ መጠን ከቦታ ቦታ ቢለያይም የወባ በሽታን በተሻለ ቅንጅት መከላከል መቻሉን ጠቅሰው ከ5 ሚሊየን በላይ በወባ ለተያዙ ዜጎች ተገቢውን ህክምና በመስጠት ማዳን መቻሉንም ዶክተር ህይወት ጠቅሰዋል።

እነዚህን ውጤታማ ተግባራት ለማሳደግ ዘንድሮ ለመጀመሪያ ጊዜ የወባ መከላከያ ክትባት በ58 ወረዳዎች መጀመሩን ጠቅሰው ክትባቱ በተለይ የህፃናትና እናቶችን ጤና ለመጠበቅ ወሳኝ እርምጃ መሆኑን አመልክተዋል።
 
የድሬዳዋ አስተዳደር ከንቲባ ከድር ጁሃር በበኩላቸው በአስተዳደሩ ወባን ለመከላከል በተሰሩ ስራዎች የተገኙ ውጤቶችን ቀጣይነት ለማረጋገጥ በቁርጠኝነት እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።


 

ከንቲባው አክለውም፤ ወባን የመከላከልና የማጥፋት ስራ ለአንድ ሴክተር ብቻ የሚተው አለመሆኑን በመገንዘብ ጤናማ ማህበረሰብን የመፍጠር ጉዞን በውጤት መደምደም ይገባል ብለዋል።

ህብረተሰቡም የወባ ትንኝ መራቢያ ስፍራዎችን በማፋሰስ፣ የአካባቢውንና የቤቱን ንፅህና በመጠበቅ እያበረከተ ያለውን አስተዋፅኦ ማጠናከር እንዳለበትም አሳስበዋል።
 
በአስተዳደሩ የወባ በሽታ በአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት የመጨመር አዝማሚያ ቢያሳይም በተከናወኑ የተቀናጁ የመከላከል ስራዎች የበሽታውን ስርጭት መቀነስ ተችሏል ያሉት ደግሞ የድሬዳዋ አስተዳደር ጤና ቢሮ ኃላፊ ዶክተር ፅጌረዳ ክፍሌ ናቸው።


 

በአስተዳደሩ  ወባ እና በወባ ንክሻ የሚተላለፉትን የደንጊና የቹኩንጊኒያ በሽታዎች ለመከላከልና ለመቆጣጠር የተሰሩ ስራዎች ውጤታማ መሆናቸውንም አክለዋል።

በስነ-ስርዓቱ የፌደራልና የክልሎች የዘርፉ አመራሮች፣ የኃይማኖት አባቶችና የሀገር ሽማግሌዎች፣ ተማሪዎች፣ በየደረጃው የሚገኙ የህብረተሰብ ክፍሎች ተሳታፊ ሆነዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም