የመሶብ አንድ ማዕከል አገልግሎት እንግልትና አላስፈላጊ ወጪን አስቀርቶልናል - ተገልጋዮች - ኢዜአ አማርኛ
የመሶብ አንድ ማዕከል አገልግሎት እንግልትና አላስፈላጊ ወጪን አስቀርቶልናል - ተገልጋዮች
ሆሳዕና፤ ሚያዝያ 17/2018 (ኢዜአ)፦ የመሶብ አንድ ማዕከል አገልግሎት እንግልት እና ያልተገባ ወጪን እንዳስቀረላቸው በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የሆሳዕና ከተማ ተገልጋዮች ገለፁ፡፡
በማዕከሉ አገልግሎት በማግኘት ላይ የነበሩት አቶ ዮናስ ሴራሞ ለኢዜአ እንደገለፁት ፤የገቢ ግብር ጉዳይ ላይ አገልግሎት ለማግኘት ወደ ማዕከሉ እንደመጡና ባጠረ ጊዜም የሚፈልጉትን ፈጽመው ለመመለስ መቻላቸውን ነው የሚገልጹት።
የመሶብ አንድ ማዕከል አገልግሎት ተገልጋይን ከአላስፈላጊ ከሆነ እንግልትና ወጪ እንደሚታደግ በተግባር ያረጋገጡ መሆኑንም ተናግረዋል።
የግብር ከፋይነት መለያ ቁጥር ለማውጣት ወደ ማዕከሉ የመጣው ወጣት ሞላልኝ ታምራት በወቅቱ አገልግሎቱን ማግኘቱን እና ማዕከሉ በአገልግሎት አሰጣጥ ላይ ይታይ የነበረውን የመልካም አስተዳደር ችግር በመቅረፍ ለማሕበረሰቡ አስፈላጊ የሆነ አገልግሎት እየሰጠ መሆኑን ነው የገለጸው።
በማዕከሉ የተገልጋዩን ክብር የጠበቀ እና ቀልጣፋ አገልግሎት ማግኝቷ እንዳስደሰታት የምትገልፀው ደግሞ ወጣት በረከት ዱቲሶ ናት፡፡
በፋይዳ መታወቂያዋ ላይ ያጋጠማትን የስም ስህተት በአጭር ጊዜ ማስተካከል ችያለሁ ብላለች።
የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል መሶብ አንድ ማዕከል አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር አቶ ከበደ ሻሜቦ ማዕከሉ በስምንት ተቋማት 27 አገልግሎቶችን እየሰጠ እንደሚገኝ ተናግረዋል፡፡
እስካሁን ድረስ ከ 20 ሺህ በላይ ለሚሆኑ ዜጎች አገልግሎት መስጠት መቻሉንም አስረድተዋል፡፡
በከተሞች በመሬት ዘርፍ የሚሰጡና ለብልሹ አሰራር ተጋላጭ የሆኑ አዳዲስ 48 አገልግሎቶች ተለይተዉ በማዕከሉ ውስጥ አገልግሎት ለመስጠት እንዲቻልም ቅድመ ዝግጅት እየተደረገ እንደሚገኝም ገልፀዋል፡፡