ቀጥታ፡

በክልሉ ባለፉት ዘጠኝ ወራት ቀልጣፋ የፍትህ አገልግሎትን ተደራሽ በማድረግ ረገድ አበረታች ውጤት ተመዝግቧል

አዳማ፤ ሚያዝያ 17/2018 (ኢዜአ)፦በኦሮሚያ ክልል ባለፉት ዘጠኝ ወራት ቀልጣፋ የፍትህ አገልግሎትን ለህብረተሰቡ ተደራሽ በማድረግ ረገድ አበረታች ውጤት መመዝገቡን  የኦሮሚያ ጠቅላይ አቃቤ ህግ ቢሮ ገለፀ።

የቢሮው የበጀት ዓመቱ ዘጠኝ ወራት ዕቅድ አፈፃፀምና የቀጣይ አምስት ዓመት ስትራቴጂክ ዕቅድ የውይይት መድረክ በአዳማ ገልመ አባገዳ አዳራሽ እየተካሄደ ነው።


 

የኦሮሚያ ጠቅላይ አቃቤ ህግ ቢሮ ኃላፊ አቶ ጉዮ ዋሪዮ እንደገለፁት፤ በክልሉ ባለፉት ዘጠኝ ወራት የህግ የበላይነትን ለማረጋገጥ በተደረገ ጥረት ቀልጣፋ የፍትህ አገልግሎትን ተደራሽ በማድረግ አበረታች ውጤት ተመዝግቧል።

በዚህም የደንበኞች የፍትህ አገልግሎት ዕርካታ ከመጨመሩም ባለፈ የክስ መዝገቦችን በማጥራትና በወቅቱ ውሳኔ እንዲያገኙ በማድረግ ስኬታማ ስራዎችን ለማከናወን ተችሏል።

በዚህም ለሌብነት፣ ለብልሹ አሰራርና ለአገልግሎት ጥራት መጓደል በር የሚከፍቱ አሰራሮችን ማስወገድ የተቻለ መሆኑንም ነው የተናገሩት።

በዚሁ ወቅት በተከናወኑት ተግባራትም በፍትህ አገልግሎት አሰጣጡ ላይ ሊኖር የሚችለውን የህብረተሰቡን ቅሬታ መፍታት መቻሉንም አስረድተዋል።

ቀልጣፋ የፍትህ አገልግሎትን ተደራሽ በማድረግ ረገድ አበረታች ውጤት የተገኘ ቢሆንም የክስ መዝገቦች ጥራት ላይ ያሉ ክፍተቶችን ለመሙላት አሰራሩን የማዘመን ተግባራት መከናወናቸውን አስረድተዋል።

አሰራሩን በቴክኖሎጂ በማስደገፍ ከወረቀት ንክኪ ነፃ የሆነ አገልግሎት ለመስጠትም የተለያዩ መተግበሪያዎች ለምተው ወደ ስራ እየገቡ መሆኑንም አብራርተዋል።

የአርሲ ዞን አቃቤ ህግ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ከማል አብዳ በበኩላቸው፤ በዞኑ የህግ የበላይነትን ለማረጋገጥና ቀልጣፋ የፍትህ አገልግሎትን ተደራሽ ለማድረግ የተደረገው ጥረት ውጤት የተገኘበት እንደሆነም አንስተዋል።


 

በተለይ በዞኑ ሴቶች፣ ህፃናትና አረጋውያንን ጨምሮ 433 መዝገቦች በነፃ የህግ ውሳኔ እንዲያገኙ በማድረግ ሁለንተናዊ የፍትህ ተደራሽነትን በማረጋገጥ ረገድ የተሻለ አፈፃፀም መመዝገቡንም አክለዋል።

ቢሮው ባለፉት ዘጠኝ ወራት በተለያዩ አካላት እጅ የነበረን ከ8 ነጥብ 6 ቢሊዮን ብር በላይ ገንዘብ ያስመለሰ ሲሆን በመንግሥት ላይ የቀረቡ ክሶችን ተከራክሮ በመርታት ከመንግስት ካዝና ይወጣ የነበረን ከ10 ቢሊዮን ብር በላይ መታደጉንም ገልጿል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም