የነዋሪዎችን ሕይወት ለማሻሻል የሚከናወኑ ዘርፈ-ብዙ የልማት ተግባራት ተጠናክረው ይቀጥላሉ - ኢዜአ አማርኛ
የነዋሪዎችን ሕይወት ለማሻሻል የሚከናወኑ ዘርፈ-ብዙ የልማት ተግባራት ተጠናክረው ይቀጥላሉ
አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 17/2018 (ኢዜአ)፦የከተማዋን ነዋሪዎች የኑሮ ሁኔታ ለማሻሻል የሚከናወኑ ዘርፈ-ብዙ የልማት ተግባራት ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለጹ።
ከንቲባ አዳነች አቤቤ በአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ በተለምዶ "ቅጠል ተራ" ተብሎ በሚጠራው አካባቢ የ500 ቤቶች ግንባታን በይፋ አስጀምረዋል፡፡
ከንቲባ አዳነች አቤቤ በዚሁ ወቅት ባስተላለፉት መልዕክት፤ ዜጎች ምቹና ክብርን የሚመጥን የኑሮ ደረጃ እንዲኖራቸው ለማስቻል መንግሥት የጀመራቸውን ሰው ተኮር የልማት ሥራዎች አጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጸዋል።
ይህም ነዋሪዎችን ለተሻለ ሕይወትና ለላቀ ተጠቃሚነት የሚያበቁ የልማት ስኬቶችን በትኩረት እያከናወነ መሆኑን የሚያረጋግጥ ነው ብለዋል።
ዛሬ የተጀመረው ዘመናዊ የመኖሪያ ቤት ግንባታም የዚሁ ጥረት አካልና የነዋሪዎችን የኑሮ ደረጃ ለማሻሻል ያለመ መሆኑን ተናግረዋል።
አካባቢው ቀደም ሲል ለኑሮ ምቹ እንዳልነበር ያስታወሱት ከንቲባዋ፣ አሁን የሚገነቡት ዘመናዊ ቤቶች ለልጆች መጫወቻ የሚሆኑ ምቹ ስፍራዎች፣ አረንጓዴ ቦታዎችና ሌሎች አስፈላጊ ማህበራዊ መሠረተ ልማቶች የተሟሉላቸው ናቸው ብለዋል፡፡
ግንባታው የአካባቢውን ገጽታ ከመቀየር ባለፈ፣ የነዋሪዎችን የዕለት ተዕለት ሕይወት የሚቀይርና በርካታ ዜጎችን ተጠቃሚ የሚያደርግ ወሳኝ የልማት ሥራ መሆኑንም አክለዋል።
በከተማዋ የቤት አቅርቦትን ለማሻሻል የሚከናወኑ ተግባራት ተጨባጭ ውጤት እያመጡ መሆኑን የጠቀሱት ከንቲባዋ፤ በቀጣይም የነዋሪውን ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ መሰል ሥራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ አረጋግጠዋል።
መንግሥት ፕሮጀክቶችን ጀምሮ የመጨረስ ልምዱን በመጠቀም ግንባታው በተቀመጠለት የጊዜ ገደብ ተጠናቆ ለተጠቃሚዎች እንደሚተላለፍም አስታውቀዋል።