በሀገራዊ ምክክሩ ዋናውን ጉባኤ ለማካሄድ የመጨረሻው ዝግጅት እየተከናወነ ይገኛል - ኢዜአ አማርኛ
በሀገራዊ ምክክሩ ዋናውን ጉባኤ ለማካሄድ የመጨረሻው ዝግጅት እየተከናወነ ይገኛል
አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 17/2018 (ኢዜአ)፦የሀገራዊ ምክክሩ የአጀንዳ ማሰባሰብ ሂደት ተጠናቅቆ ዋናውን ሀገራዊ የምክክር ጉባኤ ለማካሄድ የመጨረሻው ዝግጅት እየተከናወነ መሆኑን የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መስፍን አርዓያ ገለጹ።
በኢትዮጵያ ለዘመናት ሲንከባለሉ የቆዩ የልዩነት ሀሳቦችን በምክክር ለመፍታትና በሃሳብ የበላይነት የሚያምን ትውልድ ለመፍጠር የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን አዲስ ምዕራፍ ጀምሯል፡፡
ኮሚሽኑ በሁሉም ክልሎችና በሁለቱ የከተማ አስተዳደሮች የሚገኙ የማህበረሰብ ክፍሎችን ያሳተፈ የአጀንዳ ማሰባሰብ ሥራን ያከናወነ ሲሆን ለዋናው ሀገራዊ የምክክር ጉባኤ ተሳታፊ የሚሆኑ ተወካዮችን የመለየት ሥራ በስኬት አጠናቅቋል።
ኮሚሽኑ የተሳታፊዎች ልየታና የአጀንዳ ማሰባሰብ ሂደት፣ ከወረዳ ጀምሮ እስከ ክልሎችና ማዕከል ድረስ በግልጸኝነት የተካሄደ መሆኑን የገለጸ ሲሆን፣ በዚህም ኮሚሽኑ ወደ ዋናው ሀገራዊ የምክክር ምዕራፍ ለመሸጋገር የሚያስችለውን አስተማማኝ መሠረት ጥሏል።
ኮሚሽኑ እስካሁን ያከናወናቸው ተግባራት፣ ኢትዮጵያዊያን በውስጣዊ ጉዳዮቻቸው ላይ በነጻነት መክረው ዘላቂ ሰላምና ብሔራዊ መግባባት እንዲሰፍን የሚያስችል ታሪካዊ ዕድል የፈጠሩ መሆናቸው ይታመናል።
የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መስፍን አርዓያ ለኢዜአ እንዳሉት፤ ሀገራዊ ምክክሩ ለዘላቂ ሰላምና ጠንካራ ሀገረ መንግሥት ግንባታ መሰረት የሚጥል ነው፡፡
ምክክሩ ዜጎች በዋና ዋና ሀገራዊ ጉዳዮች መግባባት ላይ በመድረስ በማህበራዊ፣ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ዘርፎች ዘላቂ ልማትና ዕድገት ማስመዝገብ የሚችሉበትን ዕድል እንደሚፈጥር ገልጸዋል፡፡
የሀሳብ ልዩነቶችን በሰለጠነ መንገድ በንግግር መፍታት ወሳኝ ነው ያሉት ዋና ኮሚሽነሩ፤ ዜጎች በሀገራዊ ምክክሩ የተፈጠረውን ዕድል በመጠቀም ለሀገራቸው ሰላምና ልማት ገንቢ ሚና እንዲወጡ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
ኢትዮጵያውያን በምክክር ሂደቱ በክልላቸውና በሀገራቸው ያሉ ችግሮችን ነቅሰው በማውጣት ለኮሚሽኑ ማቅረባቸውን አስታውሰዋል፡፡
በሁሉም ክልሎች፣ በሁለቱ ከተማ አስተዳደሮች እና በውጭ ከሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን እና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን ጋር መካሄዱንም ጠቅሰዋል፡፡
በቀጣይ ሳምንታት በሀገር አቀፍ ደረጃ 170 ለሚደርሱ የተመረጡ አማካሪዎች ስልጠና እንደሚሰጥ ገልጸዋል፡፡
በሀገራዊ ምክክሩ ጉባኤ የሚሳተፉ ዜጎች ሁሉንም የማህበረሰብ ክፍል የሚወክሉ መሆናቸውን በማንሳት፤ ዋና ጉባኤውን ለማካሄድም የመጨረሻ ዝግጅት እየተካሄደ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡
የኢትዮጵያ ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን በአዋጅ ቁጥር 1265/2014 ከተቋቋመበት ጊዜ ጀምሮ፣ እንደ ሀገር በማያግባቡ መሰረታዊ ጉዳዮች ላይ የጋራ መግባባት በመፍጠር ረገድ በርካታ ተግባራትን ሲያከናውን መቆየቱ ይታወቃል።