ቀጥታ፡

በስፖርት የዳበሩና ተወዳዳሪ ዜጎችን ለማፍራት የማዘውተሪያ ስፍራዎችን የማስፋፋት ስራ ተጠናክሮ ቀጥሏል 

አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 17/2018 (ኢዜአ)፦ የማዘውተሪያ ስፍራዎችን በማስፋፋት የሕፃናትና ታዳጊዎችን ስፖርታዊ ብቃት፣ ጤናና ተወዳዳሪነት የሚያረጋግጡ ተግባራት ተጠናክረው መቀጠላቸውን የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለጹ።

ከንቲባ አዳነች አቤቤ የራስ ኃይሉ የስፖርት፣ ትምህርትና ስልጠና ማዕከል ዓለም አቀፍ ውድድሮችን ማካሄድ በሚያስችል ደረጃ እድሳት ተደርጎለትና አስፈላጊ መሰረተ ልማቶች ተሟልተውለት ዛሬ በድጋሚ አገልግሎት መስጠት መጀመሩን አመልክተዋል።


 

ማዕከሉ ቀደም ብሎ ተመርቆ አገልግሎት መስጠት ጀምሮ የነበረ ቢሆንም፣ ባጋጠመው የቴክኒክ ችግር ምክንያት ለተወሰነ ጊዜ አገልግሎቱ ተቋርጦ መቆየቱን አስታውሰዋል።

ይሁን እንጂ ችግሩ እንዲፈታ ከፍተኛ ትኩረት ተሰጥቶ በመሰራቱና ዓለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቁ ተጨማሪ ግብዓቶች እንዲሟሉለት ተደርጎ ለአገልግሎት ዝግጁ መሆኑን ጠቁመዋል።

ዘመናዊው ማዕከል የኦሎምፒክ ስታንዳርድን የጠበቁ የመዋኛ ገንዳዎች፣ ሁለገብ ጅምናዚየም፣ የቅርጫት ኳስ፣ የእጅ ኳስ፣ የቮሊ ቦል፣ የቦክስ እና ለማርሻል አርት ውድድሮች የሚሆኑ መሰረተ ልማቶችን አካቶ መያዙን ነው ከንቲባዋ የገለጹት።

በተጨማሪም የሚዲያ ማዕከል፣ የቴኒስና የእግር ኳስ ሜዳዎች፣ ካፌቴሪያ፣ ሱቆች እንዲሁም የመኪና ማቆሚያና መናፈሻ ስፍራዎችን ያካተተ መሆኑን አመልክተዋል።


 

ይህ ግንባታ በአካልና በአእምሮ የበለፀገ ትውልድ ለመቅረጽ የተያዘው ግብ አካል መሆኑን የገለጹት ከንቲባዋ፤ በከተማዋ መሰል የስፖርት ማዘውተሪያዎችን በማስፋፋት ህፃናትና ታዳጊዎች ስልጠና እንዲያገኙና በስፖርት የዳበሩ ተወዳዳሪ ዜጎች እንዲሆኑ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

ማዕከሉ ከዛሬ ጀምሮ ለዓለም አቀፍ ውድድሮች፣ ለልምምድና ለስልጠና ክፍት መሆኑን የገለጹት ከንቲባዋ ፤ ህዝቡ ማዕከሉን እንዲገለገልበት፣ እንዲሁም እንዲጠብቀውና እንዲንከባከበው አሳስበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም