ቀጥታ፡

ችግሮችን በምክክር በመፍታት የጋራ ሀገርን ለመገንባት የሚደረገው ጥረት ውጤታማ እንዲሆን ሚናችንን እናጠናክራለን

ወልቂጤ፤ ሚያዝያ 17/2018 (ኢዜአ)፦ ችግሮችን በምክክር በመፍታት የጋራ ሀገርን ለመገንባት የሚደረገው ጥረት ውጤታማ እንዲሆን ሚናችንን እናጠናክራለን ሲሉ ኢዜአ ያነጋገራቸው ምሁራን ገለጹ።

የወልቂጤ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ፋሪስ ደሊል (ዶ/ር) ፤ ሀገራዊ ምክክር ለዴሞክራሲያዊ ባህል ግንባታ ወሳኝ መሆኑን ጠቁመው፣ ዩኒቨርሲቲው ለሂደቱ ስኬታማነት ጥናታዊ ጽሁፎችን በማዘጋጀትና የውይይት መድረኮችን በማመቻቸት ድጋፍ እያደረገ ይገኛል ብለዋል።


 

ምክክሩ ዘላቂ ሰላምና መረጋጋት የሰፈነባት ኢትዮጵያን ለመገንባት ትልቅ መፍትሄ መሆኑን በመጥቀስ፣ ሀገራዊ አንድነትን ለማምጣት ያለውን ፋይዳ ለማሳካት ዩኒቨርስቲው አስፈላጊውን እገዛ እንደሚያደርግ አረጋግጠዋል።

በወልቂጤ ዩኒቨርሲቲ መምህር የሆኑት አቶ ከበደ ገለታ በበኩላቸው፤ የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን እያከናወነ ያለው ተግባር ሀገራዊ ችግሮችን በዘላቂነት ለመፍታት ቀዳሚው አማራጭ መሆኑን ገልጸዋል።


 

ተነጋግሮ እና ተመካክሮ እልባት ላይ መድረስ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ መረጋጋትን ያመጣል፤ ይህም በዜጎች መካከል የጋራ መተማመንን ይፈጥራል ብለዋል።

ምሁሩ አክለውም የኮሚሽኑ የሥራ ዘመን መራዘሙ ይበልጥ አሳታፊ እና የጠራ ሥራ ለማከናወን ዕድል እንደሚፈጥር ጠቁመው፣ በምክክር ምዕራፎቹ ስኬት ሁሉም ዜጋ የበኩሉን እንዲወጣ ጥሪ አቅርበዋል።

ሌላው የጅማ ዩኒቨርሲቲ መምህር ኢንጂነር ቀነኒ ኤልያስ (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ አለመግባባቶችን በውይይት የመፍታት ባህል እንዲዳብር ከመማር ማስተማር ጎን ለጎን የምክክሩን ስኬታማነት የሚያግዙ ጥረቶችን እንደሚያደርጉ ገልጸዋል።


 

ለምክክሩ ሂደት ስኬታማነት ህዝቡ የሚያደርግው በጎ አስተዋጽኦ ውጤት እንዲያመጣ በተለይ ደግሞ የዘርፉ ምሁራን ሚና ትልቅ ነው ብለዋል።

የቆዩና የማያግባቡ ችግሮች ላይ በጋራ በመምከር ሀገራዊ መግባባት እንዲፈጠር የሚደረገው ጥረት ስኬታማ እንዲሆን የሁሉም ጥረት ያስፈልጋል ያሉት ደግሞ የወለጋ ዩኒቨርሲቲ መምህር ስለሺ ታመነ (ዶ/ር) ናቸው።


 

ይህ ሂደት የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ማሳያ መሆኑን በመጥቀስ፣ በምርምር የተደገፈ ሙያዊ እገዛ ለማድረግ ዝግጁ መሆናቸውን አረጋግጠዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም