የክልሉን ህዝብ የሰላምና የልማት ተሳታፊና ተጠቃሚ የማድረግ ተግባራትን በተቀመጠላቸው ጊዜና ጥራት ማከናወን ይገባል - ኢዜአ አማርኛ
የክልሉን ህዝብ የሰላምና የልማት ተሳታፊና ተጠቃሚ የማድረግ ተግባራትን በተቀመጠላቸው ጊዜና ጥራት ማከናወን ይገባል
ባህርዳር፤ ሚያዝያ 17/2018(ኢዜአ)፦ የክልሉን ህዝብ የሰላም እና የልማት ተግባራት ተሳታፊና ተጠቃሚ የሚያደርጉ ስራዎችን በተቀመጠላቸው ጊዜና ጥራት ማከናወን ይገባል ሲሉ የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አረጋ ከበደ ገለፁ።
''አርቆ ማየት አልቆ መስራት'' በሚል መሪ ሃሳብ የክልሉ ያለፉት ዘጠኝ ወራት የፓርቲና የመንግስት ስራዎች ዕቅድ አፈፃፀም የግምገማ መድረክ በባህር ዳር ከተማ መካሄድ ጀምሯል።
ርዕሰ መስተዳድር አረጋ ከበደ በመድረኩ እንደገለፁት፤ በክልሉ የሚከናወኑ ሁሉም ተግባራት ከዚህ ቀደም ከነበረው የአሰራር ሂደት በተለየ ሁኔታ፣ በልዩ ትኩረትና በተሻለ መንገድ መፈፀም ይገባል።
በተለይም በክልሉ ሰላምን በተቀናጀ አግባብ ከማስከበር ባሻገር ህዝብ በየደረጃው የሚያነሳቸውን የልማትና የመልካም አስተዳደር ችግሮች በዘላቂነት የመፍታት ስራ ቁልፍ ተግባር ተደርጎ ሊወሰድ እንደሚገባ ነው ያሳሰቡት።
የክልሉን ህዝብ የሰላሙም ሆነ የልማቱ ግንባር ቀደም ተሳታፊና ተጠቃሚ የማድረግ ተግባራትን በተቀመጠላቸው ጊዜና ጥራት ማከናወን ይገባል ብለዋል።
እንዲሁም ነባራዊ ሁኔታውን ታሳቢ በማድረግና በመረዳት አመራሩ ሁሉን አቀፍ ውጤታማ ተግባራትን ማከናወን እንዳለበትም አስገንዝበዋል።
ለሁለት ቀናት በሚካሔደው የግምገማ መድረክ የተገኙ ስኬቶችን ከማስቀጠል ባለፈ በአፈፃፀም ወቅት የታዩ እንከኖችን በጥልቀት በማየት በቀሪ ወራት በጊዜ የለኝም መንፈስ እንዲፈፀሙ የሚያደርግ አቅጣጫ እንደሚቀመጥም አመላክተዋል።
በክልሉ የብልፅግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ፅህፈት ቤት ኃላፊ ይርጋ ሲሳይ በበኩላቸው፤ በክልሉ ባለፋት ወራት ዘላቂ ሰላምን መገንባት የሚያስችሉ ውጤታማ ተግባራት በቅንጅት ተከናውነዋል ብለዋል።
እንዲሁም ጠንካራ አመራር በመስጠት የህዝብን የልማት ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ዘርፈ ብዙ ተግባራት መከናወናቸውንም አስረድተዋል።
በየዘርፋ የተጀመሩ የልማት ስራዎችን በቀጣይ በላቀ ስኬት ማከናወን እንዲቻል አመራሩ በትኩረት ስራዎችን ማከናወን እንዳለበትም አስገንዝበዋል።
በመድረኩ በየደረጃው የሚገኙ አመራሮች እየተሳተፉ ሲሆን የመንግስትና የፓርቲ ስራዎችን በመገምገም የቀጣይ አቅጣጫ ይቀመጣል ተብሎም ይጠበቃል።