በሲዳማ ክልል በበልግ ከሚለማው ማሳ 80 ከመቶ በላይ የሚሆነው በዘር ተሸፍኗል - ኢዜአ አማርኛ
በሲዳማ ክልል በበልግ ከሚለማው ማሳ 80 ከመቶ በላይ የሚሆነው በዘር ተሸፍኗል
ሀዋሳ ፤ ሚያዝያ 17/2018 (ኢዜአ)፦ በሲዳማ ክልል በበልግ ወቅት ከሚለማው ማሳ ከ80 ከመቶ በላይ የሚሆነው በዘር መሸፈኑን የክልሉ እርሻና ተፈጥሮ ሃብት ልማት ቢሮ አስታወቀ፡፡
የክልሉ እርሻና ተፈጥሮ ሃብት ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ መምሩ ሞኬ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ በክልሉ በተያዘው የበልግ ወቅት ከ152 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በአዝርእት፣ በስራስር አትክልትና በሌሎች ሰብሎች የመሸፈን ስራ እየተከናወነ ነው፡፡
በዚህም እስካሁን ከ80 ከመቶ ሄክታር በላይ መሬት በዘር መሸፈኑን ጠቅሰው በምርት ዘመኑ ከሚለማው ማሳ ከ24 ነጥብ 1 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት እንደሚጠበቅ ተናግረዋል፡፡
በክልሉ በዋናነት ከሚለማው የአዝርእት ሰብል በቆሎ ቀዳሚ መሆኑን ያነሱት ኃላፊው ፤በበቆሎ ማሳ ውስጥ ቦሎቄን በስብጥር በመዝራት ከተመሳሳይ መሬት የተለያየ ምርት በማግኘት የአርሶ አደሩን ተጠቃሚነት የማሳደግ ስራ እየተሰራ ነው ብለዋል፡፡
የምግብ ዋስትናን በዘላቂነት የሚያረጋግጡ ድንችና ስኳር ድንችን ጨምሮ ሌሎች የስራስር ምርቶችም ከ50 ሺህ ሄክታር በላይ የማሳ ሽፋን እንዳላቸው ገልጸዋል፡፡
በልግ አብቃይ በሆኑ የክልሉ አካባቢዎች የተሻለ የዝናብ መጠን፣ ስርጭትና የአርሶ አደር ተሳትፎ መኖሩን የገለጹት ሃላፊው የዘር መዝራት ስራውን በአንድ ሳምንት ውስጥ ለማጠናቀቅ በንቅናቄ እየተሰራ ነው ብለዋል፡፡
በምርት ዘመኑ የሚጠበቀውን ምርት ለማግኘት ከማሳ እስከ ግብዓት አቅርቦት በቂ ዝግጅት መደረጉን የጠቀሱት ኃላፊው፤ 90 ሺህ ኩንታል የአፈር ማዳበሪያና 17 ሺህ ኩንታል የበቆሎ ምርጥ ዘር ለአርሶ አደሩ መሰራጨቱን ገልጸዋል፡፡
የሃዋሳ ዙሪያ ወረዳ እርሻና ተፈጥሮ ሃብት ልማት ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ አዲሱ ደሳለኝ በበኩላቸው፤ ወረዳው በልግ አብቃይ ከሆኑ የክልሉ አካባቢዎች ቀዳሚ መሆኑን ጠቅሰው ከ18 ሺህ 500 ሄክታር በላይ መሬት ሙሉ በሙሉ በዘር ተሸፍኗል ብለዋል፡፡
ከዚህ ውስጥም ከ11 ሺህ 300 በላይ ሄክታር በላይ ማሳ በበቆሎ የተሸፈነ ሲሆን የአረም፣ የተባይና በሽታ ቁጥጥርን ጨምሮ የማሳ እንክብካቤ ስራ በትኩረት እየተከናወነ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
በወረዳው የለቡ ኮረሞ ቀበሌ ሞዴል አርሶ አደር ሳሙኤል ተካራ ፤በበልግ በቆሎ በሚያለሙበት አምስት ሄክታር ማሳ ላይ ቦሎቄን በስብጥር በመዝራት ተጨማሪ ምርት ለማግኘት እየሰሩ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡
ካለፈው ዓመት ጀምሮ በቆሎን በኩታ ገጠም ማምረት መጀመራቸውን ገልጸው ይህም ማሳቸውን ለዘርም ሆነ ለአረም ስራ ምቹ እንዲሆነና ካለሙት የበቆሎ ሰብል እስከ 150 ኩንታል ምርት እንደሚጠብቁ ተናግረዋል፡፡
ሌላው የቀበሌው አርሶ አደር ናትናኤል ሁሪሶ በበኩላቸው፤ ሁለት ሄክታር ማሳቸውን በበቆሎ ዘር ሸፍነው የአረምና የማሳ እንክብካቤ ስራ እያከናወኑ እንደሚገኙ ተናግረዋል፡፡
ምርጥ ዘርና ማዳበሪያ በወቅቱ ማግኘታቸውን የተናገሩት አርሶ አደሩ የግብርና ባለሙያዎች ድጋፍም እንዳልተለያቸውና ሰብሉ በተገቢው ቁመና ላይ መሆኑን ገልጸዋል፡፡