ቀጥታ፡

በአዲስ አበባ ዓለም አቀፍ ኮከቦችን ማፍራት የሚችሉ ዘመናዊ የስፖርት መሠረተ ልማቶች ለአገልግሎት እየበቁ ነው

አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 17/2018(ኢዜአ)፦ በአዲስ አበባ በሁሉም ዘርፍ ዓለም አቀፍ ኮከቦችን ማፍራት የሚችሉ ዘመናዊ የስፖርት መሠረተ ልማቶች ለአገልግሎት እየበቁ መሆኑን ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለጹ።

ከንቲባ አዳነች አቤቤ፤ የራስ ኃይሉ የስፖርት፣ ትምህርትና ስልጠና ማዕከል ዓለም አቀፍ ውድድሮችን ማስተናገድ በሚያስችል ደረጃ በማደስና ተጨማሪ መሰረተ ልማቶችን በማሟላት ወደ አገልግሎት እንዲገባ አድርገዋል።


 

በዚሁ ወቅት እንዳሉትም፤ በአዲስ አበባ መንግስት ለስፖርት ልማት በሰጠው ልዩ ትኩረት ጥራትና ደረጃቸውን የጠበቁ የስፖርት ማዘውተሪያ ማዕከላት ተገንብተው ለአገልግሎት እንዲበቁ እየተደረገ ነው።

በአዲስ አበባ የተገነቡት ዘመናዊ የስፖርት ማዕከላትም ለመዲናዋ ተጨማሪ ውበት ከመሆናቸውም በላይ ወጣቶች ጊዜያቸውን በበጎ ስፍራ የሚያሳልፉበትን ምቹ ምኅዳር እንደፈጠረ ገልጸዋል።

የመዲናዋ ዘመናዊ የስፖርት ማዕከላትም ትውልድ የሚታነፅባቸውና ኢትዮጵያን በዓለም መድረክ የሚያስጠሩ ብቁ ስፖርተኞችን ማፍሪያ የልህቀት ማዕከላት መሆናቸውን አስገንዝበዋል።

የስፖርት ማዘውተሪያ መሰረተ ልማቶቹም አዲስ አበባ አህጉራዊና ዓለም አቀፋዊ ውድድሮችን በብቃት የማስተናገድ አቅም የሚያሳደጉ መሆናቸውን አብራርተዋል።


 

የመሰረተ ልማት ዕሴት ታክሎበት ሥራ የጀመረው የራስ ኃይሉ የዋና መሠረተ ልማትም ዓለም አቀፍ ውድድሮችን የማስተናገድ ብቃት እንዲኖረው ተደርጎ መገንባቱን አንስተዋል።

የራስ ኃይሉ የዋና መሠረተ ልማትም ብቃት ያላቸው የኢትዮጵያ ዋናተኞችን ለማፍራት ከፍተኛ ጠቀሜታ እንደሚኖረው ገልጸዋል።

በአዲስ አበባ ኢትዮጵያን በዓለም መድረክ የሚያስጠሩ ኮከቦችን ማፍራት የሚችሉ ዘመናዊ የስፖርት መሠረተ ልማቶች ለአገልግሎት እየበቁ መሆኑን ጠቅሰዋል።

ለረጅም ጊዜ አገልግሎት እንዲሰጥ ተደርጎ የተገነባውን ዘመናዊ የዋና መሠረተ ልማትም ህብረተሰቡና የሚመለከታቸው አካላት ተገቢውን ጥበቃና እንክብካቤ ሊያደርጉለት እንደሚገባ መልዕክት አስተላልፈዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም