ቀጥታ፡

በክልሉ በመኸር አዝመራ ምርታማነትን የሚያሳድጉ ግብዓቶችንና አዳዲስ አሰራሮችን ለመተግበር ልዩ ትኩረት ተሰጥቷል

ባህር ዳር፤ ሚያዝያ 17/2018(ኢዜአ)፦ በአማራ ክልል በመጪው የመኸር አዝመራ ምርታማነትን የሚያሳድጉ ግብዓቶችንና አዳዲስ አሰራሮችን ለመተግበር ልዩ ትኩረት መሰጠቱን የክልሉ ግብርና ቢሮ አስታወቀ።

ቢሮው የ2018/2019 የመኸር ሰብል ልማት የንቅናቄ መድረክ በባህር ዳር ከተማ እያካሄደ ይገኛል።


 

የቢሮው ኃላፊ ደረጀ ማንደፍሮ በመድረኩ እንደገለጹት፤ በዘንድሮው የመኸር ምርት ዘመን ምርታማነትን የሚጨምሩ ቴክኖሎጂዎችን፣ ግብዓቶችንና አዳዲስ አሰራሮችን ለመተግበር ልዩ ትኩረት ተሰጥቷል።

በምርት ዘመኑ ከ5 ነጥብ 5 ሚሊየን ሄክታር በላይ መሬት በማልማት 205 ነጥብ 5 ሚሊየን ኩንታል ምርት ለመሰብሰብ መታቀዱን ገልጸዋል።

ግብርናውን ከኃላ ቀር የአመራረት ዘይቤ በማላቀቅ ወደ ኢንዱስትሪ መር እና ለውጭ ገበያ የሚተርፍ ምርት የማምረት ሂደት ለማሳደግ በትኩረት ይሰራል ብለዋል።

ይህንን ግብ ለማሳካትም የኩታ ገጠም እርሻን ማስፋፋት፣ የግብርና ሜካናይዜሽን አሰራርን መከተልና የአፈር አሲዳማነትን በኖራ የማከም ስራዎች በስፋት እየተከናወኑ መሆኑን ኃላፊው ጠቁመዋል።


 

በክልሉ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት የአፈርና ውሃ ጥበቃ ምርምር ዳይሬክተር ተስፋዬ ፈይሳ (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ ምርታማነትን ለማሳደግ የአፈር ጤንነትን መጠበቅ ወሳኝ መሆኑን ገልጸዋል።

በክልሉ በአሲድ የተጠቃውን መሬት በኖራ ማከም ስራ ይሰራል ያሉት ዳይሬክተሩ፤ ምርምርን መሰረት ባደረገ መልኩ የኖራ፣ የተፈጥሮ ማዳበሪያ እና የቨርሚ ኮምፖስት አጠቃቀምን በማሳደግ ምርታማነትን ለመጨመር እየተሰራ መሆኑን አስረድተዋል።

በንቅናቄ መድረኩ የክልሉ የግብርና አመራሮች፣ የዘርፉ ባለሙያዎችና የአጋር አካላት ተወካዮች በመሳተፍ ላይ ይገኛሉ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም