ቀጥታ፡

አዲስ ምዕራፍ- ከዜጎች ደጃፍ እስከ እጅ ስልክ

አዲስ ምዕራፍ- ከዜጎች ደጃፍ እስከ እጅ ስልክ

በቁምልኝ አያሌው

በአንድ ሀገር ሁለንተናዊ ዕድገት ውስጥ የመንግሥት አገልግሎት ጥራት ከሰው ልጅ የደም ዝውውር ጋር ይመሰላል። በሌላ በኩልም፣ የአገልግሎት አሰጣጥ የዜጎች የሞራልና የፍትሕ ልዕልና መለኪያ ተደርጎ ይወሰዳል። መንግሥት ለዜጎቹ የሚያቀርባቸው ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ አገልግሎቶች ጥራት፣ ፍጥነትና ፍትሐዊነትም የሀገርን ፖለቲካዊ መረጋጋትና የኢኮኖሚ አቅጣጫ የሚበይኑ መጋቢዎች ናቸው።

ታዋቂው የፖለቲካል ኢኮኖሚ ምሁር ፍራንሲስ ፉኩያማ እንደሚሉት፤ "የመንግሥት ተቋማት ብቃት (State Capacity) ለኢኮኖሚ ዕድገትና ለዴሞክራሲ መረጋጋት መሠረት ነው።" መልካም አስተዳደር የሰፈነበት ሥርዓት የሕዝብ አመኔታን በመጨመርና ማህበራዊ እኩልነትን በማስፈን ለዘላቂ ሰላም የማይተካ ሚና ይጫወታል። ይህም ሀገርን በኢኮኖሚ ለማሳደግና ለማበልጸግ በሚደረገው ርብርብ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ይኖረዋል።

ሌላኛው የኢኮኖሚክስ ምሁር ጆሴፍ ስቲግሊዝ በበኩላቸው፤ "ውጤታማ መንግሥት ማለት ዜጎቹን በግልጽነትና በተጠያቂነት የሚያገለግል፣ በሂደቱም የህዝብ አመኔታን መገንባት የሚችል ነው" ሲሉ አጽንኦት ይሰጣሉ። በአንፃሩ፤ የአገልግሎት ክፍተትና የአስተዳደር ጉድለት ለሀብት ብክነት፣ ለሙስና እና ብልሹ አሰራር በር በመክፈት ዜጎችን ለከፍተኛ ምሬት በማጋለጥ አመኔታን ያሳጣል።

ይህንን እንግልት ለማቃለል ሀገራት አገልግሎትን የሚያዘምን ፈጣንና ቀልጣፋ የዲጂታል ሥርዓት እየዘረጉ ይገኛል። ኢትዮጵያም ይህንን መርህ በመከተል ዘገምተኛ አሰራር ከወለደው የ"እጅ መንሻ" (ሙስና) ልምምድ በመላቀቅ ዘመናዊና ግልጽ የዲጂታል ሽግግርን በማፋጠን ላይ ትገኛለች። ይህም ጠንካራ ኢኮኖሚ ለመገንባትና ሉዓላዊነትን የሚያጎናጽፍ ወሳኝ የልማት ምኅዳር እየፈጠረ ነው።

የመደመር መንግሥት ዕሳቤ፤ በተቋማት ግንባታና አገልግሎት ጥራት!!

በመደመር ፍልስፍና ውስጥ የመንግሥት ተቋማት ግንባታ የሀገር ግንባታ የጀርባ አጥንት ተደርገው ይወሰዳሉ። ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በመደመር መንግሥት መጽሐፋቸው ገፅ-129 እንዳሰፈሩት፤ ''የመደመር መንግሥት ከውስብስብ ቢሮክራሲ ተላቀው የመደመር ለውጥ የሚያመጡ ተቋማት ውቅር ነው። በመሆኑም ተቋማት ከተለመደ ''የሥራ ሂደት መር'' አካሄድ መላቀቅ ይጠበቅባቸዋል። አደረጃጀታቸውንም ለሚያገለግሉት ሕዝብ ትርጉም ያለው ለውጥ እንዲያገኙ ወደሚረዳቸው አደረጃጀት መሸጋገር አለባቸው። ለመደመር መንግሥት ሕዝቡን ማገልገል ከቢሮክራሲ በላይ ነው'' በሚል አስገንዝበዋል። ለዚህም ነው ተቋማት የሰውን ልጅ አቅምና ዕውቀት አቀናጅተው ለጋራ ዓላማ የሚያውሉ ሕያው መዋቅሮች ናቸው የሚባለው።


 

በመደመር ዕሳቤ ጠንካራ ተቋማት ማለት በግለሰቦች ፍላጎትና ስሜት ላይ ያልተመሰረቱ ይልቁንም በሕግና በሥርዓት የሚመሩ መሆን አለባቸው። በመደመር መንግሥት መፅሐፍ ገፅ-130 እንደሰፈረው፤ ''በየተቋማት ያሉ የመንግስት ሠራተኞች ሕዝቡን ከቢሮክራሲው በላይ የሚመለከቱ እንዲሆኑ ይጠበቃል። አገልጋይነትን የተላበሱ መሆን ይጠበቅባቸዋል።'' መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎትም ይህንን ዕሳቤ በተግባር የሚተረጉም ነው። ግለሰባዊ ንክኪን በመቀነስና አሰራርን በቴክኖሎጂ በመተካት ተቋማት ከግለሰቦች መልካም ፈቃድ ይልቅ በሥርዓት ወደሚመራ ተቋማዊ ብቃት መሸጋገርን ያሳያል።

የአገልግሎት ጥራትና የዜጎች ክብር በመደመር መንግሥት ትልቅ ትኩረት የተሰጠው ሰው ተኮር የልማት ነጥብ ነው። ''ለሕዝቡ ቅድሚያ የማይሰጥ አመራርም ሆነ ሠራተኛ የመደመር መንግሥት ወገን አይደለም። እንዲህ ዓይነቱን ግለሰብም ሆነ አይቶ እንዳላየ በማለፍ የማይታገል ሰው በመደመር መንግሥት ውስጥ ዕድል ፈንታ የለውም'' በሚል በመደመር መንግሥት መፅሐፍ የሰፈረው ግልፅ መልዕክትም መንግሥት የአገልጋይነት እንጂ የገዥነት መንፈስ ሊኖረው እንደማይገባ በጉልህ ያመላክታል።

የአገልግሎት ጥራት መሻሻልም ዜጎች በሀገራቸው ተቋማት ክብራቸውና መብታቸው ተጠብቆ ያለ እንግልት የሚገለገሉበትን ምኅዳር ይፈጥራል። በተቋማት አገልግሎት የዜጋ እርካታ (Citizen Satisfaction) ዋነኛ የፖለቲካል ኢኮኖሚ ዕድገት ምንጭ ተደርጎ ይወሰዳል። በመደመር መንግስት ዕይታ የብልሹ አሰራር መታገያ ስትራቴጂ በጩኸትና በቅጣት ብቻ የሚመጣ ሳይሆን አሰራርን በማዘመን ጭምር ነው። የመሶብ ዲጂታል የአንድ ማዕከል አገልግሎትም ሌብነትን የማይጋብዝ ሥርዓት የፈጠረ (Systemic Prevention) ስትራቴጂክ አቅጣጫ ሆኗል።


 

የኢትዮጵያ የዲጂታል ልማትና የመሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት የመደመር መንግሥት መሠረታዊ የተቋማት ሪፎርም ትግበራን (Institutional Reform) የሚያሳዩ ናቸው። ይህም ተቋማትን ከመዋቅራዊ ሽግግርና ለውጥ ባለፈ የተቋማት ሠራተኞችን ከመንግሥት ሠራተኛነት ወደ ሕዝብ አገልጋይነት የአስተሳሰብ ለውጥ (Paradigm Shift)፣ ኋላ ቀር አሰራርን በዲጂታል የቴክኖሎጂ አማራጭ የሚተካ (Technology Integration)፣ አገልግሎትን ለሁሉም ዜጋ በእኩልነት፣ በቅርበትና ፍትሐዊነት የማዳረስ ፅንሰ ሃሳባዊ ግብን በተግባር ያረጋገጠ ሆኗል። ይህ ታላቅ ተግባርም ኢትዮጵያ በመደመር ዕሳቤ የጀመረችውን የብልፅግና ጉዞ የሚያፋጥንና ዜጎች በመንግሥታቸው ላይ ያላቸውን አመኔታ በጽኑ መሠረት ላይ የሚገነባ መሠረት ነው።

የዲጂታል ኢትዮጵያ ርዕይና ስትራቴጂክ ሽግግር!!

ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያው ለግብርና፣ ኢንዱስትሪ፣ ማዕድን፣ ቱሪዝምና አይሲቲ ዘርፎች ወሳኝ የልማት ዕድሎችን ፈጥሯል። በዚህ ሰፊ መርሃ ግብር ውስጥ የዲጂታል ኢኮኖሚ ግንባታ እንደ ዋነኛ የብልፅግና ምሰሶ ተወስዷል።

በ"ዲጂታል ኢትዮጵያ-2025" ስትራቴጂ የተጀመረውና በስኬት የተጠናቀቀው ጉዞ ዛሬ ላይ ሀገሪቷን ወደ "ዲጂታል ኢትዮጵያ-2030" አሸጋግሯታል። ይህ ስትራቴጂ ዜጎች ካሉበት ቦታ ሆነው አገልግሎት የሚያገኙበትን ምኅዳር በመፍጠር በሰው ንክኪ የሚፈጠሩ ብልሹ አሰራሮችንና የአገልግሎት እንግልትን በማስቀረት ረገድ ታሪክ ቀያሪ ሚና እየተጫወተ ይገኛል።

የልማትና ዕድገት ምሁሩ አማርትያ ሴን፤ "ልማት የሰው ልጅ ምርጫና የመገልገያ አቅሙን ማስፋፊያ መሣሪያ ነው" በማለት የሚገልጹት ስለልማት ከፍ ያለ ትርጉም ይሰጠናል። የኢትዮጵያ መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎትም ዜጎች የሚያጋጥሟቸውን እንግልቶች በማስወገድ ትኩረታቸውን በልማት ላይ እንዲያደርጉ በማስቻሉ፣ ይህንን የልማት ፅንሰ-ሃሳብ በተግባር እየተረጎመ ይገኛል።


 

የአንድ ጣሪያ በረከትና የቅልጥፍና ተምሳሌት - መሶብ

በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ሚያዚያ 18/2017 ዓ.ም የተመረቀው የፌዴራል መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት፣ ለተቋማዊ ሽግግር መነሻ ሆኗል። ቁልፍ የመንግሥት አገልግሎቶች በአንድ ጣሪያ ስር መሰባሰባቸው የአገልግሎት አሰጣጥ ጥራቱን ወደ ከፍተኛ ደረጃ አሸጋግሮታል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በወቅቱ እንደገለጹት፤ ይህ ማዕከል ዜጎች ጊዜያቸውንና ሀብታቸውን በመቆጠብ ጥራት ያለው አገልግሎት እንዲያገኙ በማድረግ ለዘመናት የቆየውን ምሬት የሚቀለብስ የሪፎርም እርምጃ ነው።  በወቅቱ ሲጀመር 12 የነበሩት ፌዴራል ተቋማት፤ አሁን ላይ 23 በመሻገር አገልግሎታቸውን እየሰጡ ይገኛል። ይህም የዜጎች እንግልት በማስቀረት ታላቅ እፎይታን ፈጥሯል።

እነዚህ ተቋማት፦ የብሔራዊ መታወቂያ፣ የኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት፣ የሰነዶች ማረጋገጫና ምዝገባ አገልግሎት፣ የገቢዎች ሚኒስቴር፣ የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር፣ የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር፣ የኢንቨስትመንት ኮሚሽን፣ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር፣ የትምህርት ስልጠና ባለስልጣን፣ ኢትዮ ፖስታ፣  ኢትዮ ቴሌኮም፣ የመንግስት ግዥና ንብረት ባለስልጣን፣ የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስቴር፣ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ፣ የአካባቢ ጥበቃ ባለስልጣን፣ የኢትዮጵያ ምግብና መድኃኒት ባለስልጣን፣ የኢትዮጵያ ግብርና ባለስልጣን፣ የኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ባለስልጣን፣ የኢትጵያ ጉምሩክ ኮሚሽን፣ የጤና ሚኒስቴር፣ የፍትሕ ሚኒስቴር፣ ቱሪዝም ሚኒስቴር፣ የትምህርት ምዘናና የፈተናዎች አገልግሎት ናቸው።

መነሻውን አዲስ አበባ ከተማ የፌዴራል ተቋማት በአንድ በማሰባሰብ የጀመረው ይህ አገልግሎት አሁን ላይ በሁሉም ክልሎችና በሁለቱ የከተማ አስተዳደሮች ተደራሽ እየሆነ ነው። ይህም የመልካም አስተዳደር እጦትን የሚያቃልል ታሪክ ቀያሪ መደላድል ፈጥሯል።

አዲስ መሶብ - የተንቀሳቃሽ አገልግሎት ተስፋ!!

በመዲናችን ሚያዚያ 14 ቀን 2018 ዓ.ም በይፋ የተጀመረው መሶብ የአንድ ማዕከል ተንቀሳቃሽ አገልግሎት፣ "መንግሥት ወደ ዜጋው ይሄዳል" (Citizen-Centric Governance) የሚለውን የዘመናዊ አስተዳደር ፍልስፍና በተግባር ያሳየ ነው። በፀሐይ ኃይልና በፈጣን ኔትወርክ የታገዘው ይህ ተንቀሳቃሽ አገልግሎት የስምንት ተቋማትን 36 ዓይነት አገልግሎቶች ወደ ህዝቡ ደጃፍ በማምጣት ረገድ ተምሳሌት ሆኗል።


 

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ በወቅቱ እንደገለጹት፤ ከተማዋ ለዘመናት ስር በሰደደ የአገልግሎት አሰጣጥ ችግር ተተብትባ ብትቆይም፣ የመሶብ  ዲጂታል አገልግሎት ግን ለተገልጋዩ እውነተኛ እፎይታን ይዞ መጥቷል።

የቀጣዩ ዘመን ግብ - አገልግሎትን በእጅ ስልክ!!

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በቀጣይ አገልግሎቱን ወደ ዜጎች የእጅ ስልክ የማሸጋገር ግብ መኖሩን አረጋግጠዋል። ይህ ሽግግር ሙሉ በሙሉ ስኬታማ እንዲሆን የዲጂታል መታወቂያ ወሳኝ ሚና ይጫወታል። ዜጎችን በዲጂታል መታወቂያ መለየት መቻሉ የአሰራር ግልጽነትን ከመጨመሩም በላይ መንግሥት አገልግሎቱን ለማን እየሰጠ እንደሆነ በትክክል እንዲያውቅ ያስችለዋል።


 

ተገልጋይን አክብሮ፣ ስርቆትና "እጅ መንሻን" አስቀርቶ አገልግሎት መስጠት የባህል ለውጥ ይጠይቃል። ለዚህም ሲቪል ሰርቪሱን በማዘመን፣ ቴክኖሎጂንና የባህል ለውጥን በማቀናጀት የእጅ መንሻን ባህል የሚያስቀር መሠረት እየተጣለ ይገኛል። ለዚህ ለውጥ ስኬት እያንዳንዱ ዜጋና ተቋም የበኩሉን ሊወጣ ይገባል። 

በአጠቃላይ የኢትዮጵያ የዲጂታል ልማት መርሃ ግብርና የመሶብ አንድ ማዕከል አገልግሎት ሙስናን በማድረቅ ፍቱን መፍትሔ እየሰጡ ይገኛሉ። ይህም ሀገሪቷን ከቆየችበት የ"እጅ መንሻ" አዙሪት አውጥቶ፣ ተቋማት ለዜጎች ክብር ወደሚያሳዩበት አዲስ ምዕራፍ አሸጋግሯታል። ይህ ጉዞ እመርታ ነው፤ ግልጽነትን በማንገስና የህዝብን እርካታ በመጨመር የብልጽግና ጉዞውን የሚያፋጥን ነው።  

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም