የምርጫ ፍትህ መረጋገጥ ለዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ወሳኝ መሰረት ነው - ኢዜአ አማርኛ
የምርጫ ፍትህ መረጋገጥ ለዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ወሳኝ መሰረት ነው
አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 17/2018(ኢዜአ)፦ የምርጫ ፍትህ መረጋገጥ ለዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ወሳኝ መሰረት መሆኑን የፌዴራል ሕግና ፍትህ ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር አምባሳደር ደግፌ ቡላ ገለጹ።
የምርጫ ፍትህን ለማረጋገጥ የተቀናጀ የተቋማት ሚና ወሳኝ መሆኑንም ዋና ዳይሬክተሩ ጠቅሰዋል።
የፌዴራል ሕግና ፍትህ ኢንስቲትዩት "የምርጫ ፍትህ (Electoral Justice) በኢትዮጵያ የዳኝነት፣ የፍትህ እና የአስተዳደር አካላት ሚና" በሚል መሪ ሃሳብ ያዘጋጀው የምርምር ኮንፈረንስ እየተካሄደ ነው።
የኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር አምባሳደር ደግፌ ቡላ በዚሁ ጊዜ እንደተናገሩት፤ ኢንስቲትዩቱ በየወሩ በተለያዩ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ የውይይት መድረኮችን በማዘጋጀት የሕግ ባለሙያዎችና የህብረተሰቡ ግንዛቤ እንዲዳብር በስፋት እየሠራ ይገኛል።
የምርጫ ፍትህ ርዕሰ ጉዳይ የተመረጠው የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ መሠረት በመሆኑ ነው ብለዋል።
በሀገራችን ለሰባተኛ ጊዜ ለሚካሄደው ጠቅላላ ምርጫ ከፍተኛ ርብርብ እየተደረገ ባለበት በዚህ ወቅት የምርጫ ፍትህ ላይ መምከር ወቅታዊና አስፈላጊ መሆኑን ጠቁመዋል።
ዴሞክራሲን እንደ አንድ የተሳሰረ ሥርዓት መመልከት እንደሚገባና በዚህ ሂደት ውስጥ የምርጫ ቦርድ፣ የፖሊስ፣ የዓቃቤ ሕግና የፍትህ አካላት ሚና የማይነጣጠል መሆኑን አጽንኦት ሰጥተዋል።
የምርጫ ሂደት ስኬታማ እንዲሆን ተቋማት ብቻ ሳይሆኑ እያንዳንዱ ዜጋ የበኩሉን ሚና መወጣት እንዳለበትም አስገንዝበዋል።