ቀጥታ፡

በዞኑ የቡና ምርታማነትን ለማሳደግ የሚያስችል 70 ሚሊዮን የተሻሻለ የቡና ችግኝ ለተከላ ተዘጋጅቷል

አዶላ፤ ሚያዝያ 17/2018 (ኢዜአ)፦ በኦሮሚያ ክልል ጉጂ ዞን የበልግ ዝናብ ወቅትን በመጠቀም የቡና ምርታማነትን ለማሳደግ የሚያስችል 70 ሚሊዮን የተሻሻለ የቡና ችግኝ ለተከላ መዘጋጀቱን  የዞኑ ግብርና ጽህፈት ቤት አስታወቀ።

በጽህፈት ቤቱ የቡናና ሻይ ልማት ባለሙያ አቶ ብርሀኑ ፈይሳ እንደገለጹት፤ ዘንድሮ የተዘጋጀው የቡና ችግኝ ከቀደሙት ዓመታት ብልጫ እንዳለው ጠቅሰው፤ በዞኑ ሁሉም ወረዳዎች የበልጉን ዝናብ በመጠቀም እስካሁን በ9 ሺህ 300 ሄክታር መሬት ላይ ተከላ የመከናወኑን ገልጸዋል፡፡

በዚህም ከ40 ሺህ በላይ አርሶ አደሮች መሳተፋቸውን ተናግረዋል።


 

እየተተከሉ ያሉ ችግኞች አብዛኞቹ ከግብርና ምርምር ማዕከላት የተገኙና ከአካባቢ ዘር የተዘጋጁ መሆናቸውንም ባለሙያው ገልጸዋል። 

የችግኝ ዝርያዎቹ በተለይም ከጅማ ግብርና ምርምር ማዕከል፣ ከይርጋለም እና ከአወዳይ ግብርና ምርምር ጣቢያዎች የተለቀቁ መሆናቸውንም ነው የገለጹት።

እየተተከሉ ያሉ ዝርያቸው የተሻሻለ የቡና አይነቶች በሄክታር ከ12 እስከ 15 ኩንታል ምርት መስጠት የሚችሉ መሆኑን ገልጸው፤ በነባሩ ዝርያ የሚገኘው ምርት ከ6 ኩንታል ያነሰ እንደነበር  አስታውሰዋል።

የተተከለው ችግኝ ከአምስት ዓመት ባነሰ ጊዜ ውስጥ ምርት መስጠት የሚጀምር ሲሆን፣ ነባሩ ዝርያ ምርት ለመስጠት ከ7 እስከ 8 ዓመት ይፈጅበታል ብለዋል።

በዞኑ ውስጥ ለቡና ልማት ተስማሚ የሆነ ከ10 ሺህ 600 ሄክታር በላይ መሬት መዘጋጀቱንና የዞኑ አርሶ አደሮችም ከሰብልና ከእንስሳት እርባታ ጎን ለጎን በቡና ልማት ላይ እየተሳተፉ እንደሚገኙ አስታውቀዋል።

በዞኑ በ12 ወረዳዎችና በ157 ቀበሌዎች ከ177 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በቡና ልማት የተሸፈነ መሆኑንም አመልክተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም