በምዕራብ ሸዋ ዞን በአፕል ልማት የተሰማሩ አርሶ አደሮች ተጠቃሚነታቸው እያደገ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በምዕራብ ሸዋ ዞን በአፕል ልማት የተሰማሩ አርሶ አደሮች ተጠቃሚነታቸው እያደገ ነው
አምቦ፤ ሚያዝያ 17/2018 (ኢዜአ)፦በምዕራብ ሸዋ ዞን በአፕል ልማት ላይ የተሰማሩ አርሶ አደሮች ከምርቱ በሚያገኙት ገቢ ተጠቃሚነታቸው ማደጉን ገለጹ።
የዞኑ ግብርና ጽህፈት ቤት በበኩሉ በዞኑ ለፍራፍሬ ልማት ልዩ ትኩረት ተሰጥቶ በተሰራው ስራ ውጤት እየተገኘ መሆኑን አረጋግጧል።
ቀደም ሲል በዞኑ የፍራፍሬ ልማት ያልተለመደ ቢሆንም፣ ባለፉት ጥቂት ዓመታት በተደረገ የተቀናጀ ጥረት አርሶ አደሩ ከጥራጥሬ ሰብሎች በተጨማሪ በፍራፍሬ ልማት በመሰማራት ገቢውን እያሳደገ ይገኛል።
በዞኑ የጅባትና የሚዳቀኝ ወረዳ አርሶ አደሮች ከግብርና ባለሙያዎች ያገኙትን የሙያና የችግኝ ድጋፍ ተጠቅመው ወደ ስራ መግባታቸውንና ውጤታማ መሆናቸውን ጠቅሰዋል።
የጅባት ወረዳ አርሶ አደር ሀይሉ ኢትቻ "በአፕል ልማት በመሳተፍ ምርቱን ለገበያ በማቅረብ የተሻለ ገቢ እያገኘሁ ነው'' ብለዋል።
ልማቱን ቀደም ብለው በመጀመራቸው የአፕል ምርት ልምዳቸውን ለአካባቢው አርሶ አደሮች እያካፈሉ መሆኑንም ተናግረዋል።
ሌላው የሚዳቀኝ ወረዳ አርሶ አደር ደረጄ አብሼ፤ በባለሙያዎች የተሰጣቸውን ግንዛቤና ክትትል ተጠቅመው የአፕል ተክሉን በመንከባከባቸው ተጠቃሚ መሆን መጀመራቸውን ተናግረዋል። ከአፕል ልማት በሚያገኙት ተጨማሪ ገቢ ልጆቻቸውን በተሻለ ሁኔታ እያስተማሩ መሆናቸውን ገልጸዋል።
በዞኑ ግብርና ጽህፈት ቤት የአትክልትና ፍራፍሬ ልማት ባለሙያ የሆኑት አቶ መንገዱ ጉርሙ እንደገለጹት፤ በአሁኑ ወቅት በዞኑ ጅባት፣ ሚዳቀኝ፣ ኢልፋታ፣ አምቦ እና ወልመራ አፕል በስፋት የሚመረትባቸው ወረዳዎች ሲሆኑ፣ በሌሎች ወረዳዎችም እንደየአየር ንብረታቸው ልማቱን የማስፋፋት ስራ እየተከናወነ ይገኛል።
በአሁኑ ወቅት በዞኑ በ3 ሺህ 110 ሄክታር መሬት ላይ የተለያዩ ፍራፍሬዎች እየለሙ ሲሆን፣ ከዚህ ውስጥ 265 ሄክታሩ በአፕል የተሸፈነ ነው ብለዋል።
በአፕል እየለማ ከሚገኘው መሬትም እስካሁን ባለው ሂደት 11 ሺህ 720 ኩንታል መሰብሰብ ተችሏል ነው ያሉት።
አርሶ አደሩን ይበልጥ ተጠቃሚ ለማድረግ የዞኑ ግብርና ጽህፈት ቤት ከወረዳ ግብርና መዋቅሮችና ከባለድርሻ አካላት ጋር በመተባበር የተሻሻሉ ዝርያዎችን በማቅረብና ስልጠናዎችን በመስጠት ላይ መሆኑንም ተናግረዋል።