ቀጥታ፡

በምስራቅ ወለጋ ዞን የ2018/19 የምርት ዘመን ምርታማነትን ለማሳደግ ለአርሶአደሮች ግብዓት እየቀረበ ነው 

ነቀምቴ ፤ ሚያዝያ 17/2018 (ኢዜአ)፦ በምስራቅ ወለጋ ዞን የ2018/19 የምርት ዘመን ምርታማነትን ለማሳደግ የግብዓት አቅርቦት ላይ ትኩረት መደረጉን የዞኑ ግብርና ፅህፈት ቤት አስታወቀ።

በዞኑ ግብርና ፅህፈት ቤት የግብዓት አቅርቦት እና ፍላጎት ቡድን መሪ አቶ ለሚ አጋ፤ የአርሶ አደሩን የግብዓት ፍላጎት በመለየት መጪውን የምርት ዘመን ውጤታማ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።


 

በዚህም 463 ሺህ 744 ኩንታል ማዳበሪያ ወደ ዞኑ መግባቱን ገልጸው 311 ሺህ 877 ኩንታሉ ለአርሶ አደሩ ለማሰራጨት ተችሏል ነው ያሉት።

እንዲሁም ከምርጥ ዘር ጋር በተያያዘም ከ13 ሺህ ኩንታል በላይ የቀረበ ሲሆን ከ10 ሺህ ኩንታል በላይ የሚሆነው ለአርሶ አደሩ መቅረቡን ገልጸዋል።

በዘንድሮው የምርት ዘመን ከ203 ሺህ 825 አርሶ አደሮች በላይ የሚሳተፉ ሲሆን ከ800 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት ይለማል ተብሎ እንደሚጠበቅ አቶ ለሚ ተናግረዋል።

በዞኑ በቆሎ፣ ማሽላ፣ ጤፍ፣ ሱፍ እና ሰሊጥ በስፋት የሚመረት መሆኑን ጠቁመው የምርት ማሳደጊያ ግብዓቶቹን ለአርሶ አደሩ በፍትሃዊነት ተደራሽ በማድረግ ላላስፈላጊ ወጪ እንዳይዳረግ እየተሰራ ነው ብለዋል።

የዞኑ አርሶ አደሮችም መንግስት ከወዲሁ ምርታማነትን ለማሳደግ ትኩረት ሰጥቶ በመስራት ያደረገው ቅድመ ዝግጅት እንዳስደሰታቸው ገልጸዋል።


 

በዞኑ ኡኬ ከተማ ነዋሪና አርሶ አደር አቶ ጫሊ ከበደ ፤ባላቸው 30 ሄክታር መሬት ላይ በእርሻ ኢንቨስትመንት መሰማራታቸውን ገልጸው ለስራው አስፈላጊ የሆነውን ግብዓት እያገኙ መሆናቸውን አስረድተዋል።

በወረዳው ያለውን ምቹ የአየር ንብረት እና ለም መሬት በመጠቀም በስፋት በቆሎ በማምረት ላይ እንደሚገኙም ገልጸዋል።


 

አርሶ አደር አቶ ተመስገን ሁንደራ፤ ባላቸው ዘጠኝ ሄክታር መሬት ላይ በቆሎ በማምረት ላይ እንደሚገኙ ተናግረው የምርት ማሳደጊያ እያስገቡ መሆኑንም ጠቁመዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም