ቀጥታ፡

የጤና ነገር …

በዮሐንስ ደርበው

• የቆዳ ካንሰርን ቀድሞ መከላከል ይቻላል?

የቆዳ ካንሰር መንስዔ ምንድን ነው? ቀድሞ መከላከልስ ይቻላል? ሕክምናውስ ምንድን ነው? በሚሉትና ተያያዥ ጉዳዮች ላይ የሥነ-ውበት ባለሙያ የሆኑት ዶክተር ሱመያ ኑርሁሴን ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቆይታ ሙያዊ ማብራሪያ ሰጥተዋል።

• አጠቃላይ መነሻ

እንደ ዶክተር ሱመያ ገለጻ፤ በአጠቃላይ ሦስት ዓይነት የቆዳ ካንሰሮች እንዳሉ ይታመናል። አንዳንዶቹ ከቆዳ አልፈው ወደ ውስጠኛው የሰውነት ክፍል የመስፋት ዕድል እንዳላቸውም ያነሳሉ።

የቆዳ ካንሰር ቆዳ ላይ ያሉ ኅዋሶች ዲ ኤን ናቸው (DN) በፀሐይ ጨረር እና በተለያዩ ምክንያቶች ሲጎዳ የቆዳ ኅዋሶች ከቁጥጥር ውጭ በሆነ ሁኔታ ራሳቸውን በማባዛት መደበኛውን ሥርዓት ሲያዛቡ የሚከሰት የቆዳ ህመም መሆኑን አስረድተዋል።

በሰውነት ላይ ያሉ ኅዋሶች (ሴሎች) ራሳቸውን ያድሳሉ ያሉት ባለሙያዋ፤ ይህን የሚያድሱበት ሥርዓት በሚዛባበት ጊዜ ቆዳ ላይ ያሉ ኅዋሶች ከቁጥጥር ውጭ በሆነ መንገድ ይዛባሉ ሲሉም አብራርተዋል። በሚዛቡበት ጊዜም መደበኛ የነበረው ኅዋስ ወደ ካንሰር ኅዋስ ይቀየራል።

• መንስዔ

ዋነኛው የቆዳ ካንሰር መንስዔ ለረጂም ጊዜ ለከፍተኛ የፀሐይ ጨረር መጋለጥ መሆኑን የሚገልጹት ዶክተር ሱመያ፤ በተጨማሪም ሥር የሰደዱ ቁስሎች እንዲሁም በሕክምና ባለሙያ ያልተደገፉ ኬሚካሎችና ክሬሞች መጠቀም ለቆዳ ካንሰር እንደሚያጋልጥ አስገንዝበዋል።

በሌላ በኩል በዘር (በቤተሰብ) በቆዳ ካንሰር የተጠቃ ካለም የመተላለፍ ዕድል እንዳለውን ገልጸዋል።

• ምልክቶች

ዶክተር ሱመያ ሲያብራሩ፤ አጠቃላይ በባለሙያዎች አጠራር የቆዳ ካንሰር ምልክቶች (A,B,C,D,E) በሚል አጠራር በሕክምናው እንደሚለዩ ጠቁመዋል። ይህ ማለትም፤ አሴሚትሊ፣ ቦርደር፣ ከለር፣ ዳያሜትር፣ ኢንቮልቪንግ እንደሆነ ተናግረዋል።

ከቆዳ ካንሰር ምልክቶች መካከልም፤ ወጣ ገባ ያለ (ተመሳሳይ ቅርጽ የሌለው የቁስል ቅርጽ)፣ የቁስሉ ጠርዝ ወጣ ገባ ያለ ከሆነ፣ በውል የማይታወቅ ጠርዝም ከሆነ፣ አንድ ቦታ ላይ የተለያየ ቀለም ያለው ቁስለት ለምሳሌ፡- ጠቆር ያለ፣ ቀላ ያለ ወዘተ…ሌላም፣ የቁስሉ ርዝመት ለምሳሌ፡- ከጎን እና ጎን ያለው ስፋት ከ6 ሚሊ ሜትር በላይ ከሆነ፣ ከጊዜ ወደ ጊዜ መጠኑ እየጨመረ፣ ቀለሙም እየተዛባ፣ ከጊዜ በኋላ እያደገ የሚሄድ የቁስል ዓይነት መኖር የሚሉትን ጠቅሰዋል።

• ሕክምና

የቆዳ ካንሰር ይድናል ወይስ አይድንም? ለሚለው ሐሳብ ወሳኙ ጉዳይ ህመሙ (ኬዙ) ያለበት ደረጃ መሆኑን በአጽንዖት አንስተዋል።

ለምሳሌ ይላሉ ዶክተር ሱመያ፤ የመጀመሪያዎቹ ደረጃ ላይ ከሆነ ይድናል፤ ደረጃው ከፍ ካለ ግን ኬሞቴራፒም ሬዲዮ ቴራፒም እንዲሁም የጨረር ሕክምና ሊያስፈልገው ይችላል።

የቆዳ ካንሰር ሕክምና በሀገር ውስጥ እንደሚሰጥም ተናግረዋል።

• ምክረ ሐሳብ

እንደሌሎቹ የካንሰር ዓይነቶች ስለ ቆዳ ካንሰር ብዙም አይወራም ያሉት ዶክተር ሱመያ፤ ይህን ተከትሎ የሚደረገው ጥንቃቄ እምብዛም ነው፤ ይህም በሕብረተሰቡ ዘንድ በጉዳዩ ላይ ያለው ግንዛቤ ዝቅተኛ እንዲሆን አድርጓል ይላሉ።

ይህን ሲያብራሩም፤ ለምሳሌ፡- በቆዳ ላይ ቁስል ሲወጣ አቅልሎ ማየት (ይህማ በሆነ ነገር…በጤናዳም ይድናል፣ ይህማ የቆዳ መድረቅ ነው ቫዝሊን ቀቡት፣ ይህማ ማዲያት ነው…) እየተባለ በቸልተኝነት የሚታለፍ ሁኔታ አለ ብለዋል።

ስለዚህ የግንዛቤ እጥረት ሰዎች በቀላሉ ቶሎ መዳን የሚችለውን የቆዳ ካንሰር ከተወሳሰበና የመጨረሻ ደረጃ ላይ ከደረሰ በኋላ እንዲባንኑ ያደርጋል ሲሉ ገልጸዋል።

በአጠቃላይ ቆዳ ላይ የተለየ ነገር ሲኖር ቶሎ ወደ ሕክምና ተቋም መሄድ፣ በሕክምና ባለሙያ የሚመከሩ የፀሐይ መከላከያ ክሬሞችን መጠቀም፣ ቆዳ ላይ ቁስል ሲከሰት በቶሎ ምርመራ ማድረግ እንደሚገባ በመምከር፤ ቸልተኝነት የከፋ ጉዳት ሊያስከትል እንደሚችል አመላክተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም