ቀጥታ፡

የሴቶች ፕሪሚየር ሊግ የ22ኛ ሳምንት ተጠባቂ ጨዋታዎች 

አዲስ አበባ፤ ሚያዚያ 17/2018(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪሚየር ሊግ 22ኛ ሳምንት ሁለት ጨዋታዎች ዛሬ ይካሄዳሉ።

ቀን ሰባት ሰአት ላይ ባህርዳር ከተማ ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ጋር በአበበ ቢቂላ ስታዲየም ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።

ባህርዳር ከተማ በሊጉ ባደረጋቸው 21 ጨዋታዎች አምስት ጊዜ ሲያሸንፍ 15 ጊዜ ተሸንፏል። በቀሪው አንድ ጨዋታ አቻ ተለያይቷል። በጨዋታዎቹ ላይ 10 ግቦችን ሲያስቆጥር 26 ጎሎችን አስተናግዷል። 

ቡድኑ በ16 ነጥብ 11ኛ ደረጃን ይዟል። 

ተጋጣሚው ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በበኩሉ በሊጉ 21 ጨዋታዎች አድርጎ በ17ቱ ድል ሲቀናው የተሸነፈው አንድ ጊዜ ብቻ ነው። በቀሪ ሶስት ጨዋታዎች ነጥብ ተጋርቷል።  59 ግቦችን ከመረብ ላይ ሲያሳርፍ ስምንት ግቦች ተቆጥረውበታል። 

የወቅቱ የሊጉ አሸናፊ ንግድ ባንክ በ54 ነጥብ አንደኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል።

በሌላኛው መርሐ ግብር ከቀኑ 9 ሰዓት ላይ አርባምንጭ ከተማ ከኢትዮ ኤሌክትሪክ ጋር በአበበ ቢቂላ ስታዲየም ጨዋታቸውን ያደርጋሉ። 

አርባምንጭ ከተማ በሊጉ ካደረጋቸው 18 ጨዋታዎች መካከል ሁለት ጊዜ ሲያሸንፍ በ15ቱ ሽንፈት አስተናግዷል። በአራት ጨዋታዎች ላይ አቻ ተለያይቷል። በጨዋታዎቹ 10 ግቦችን ሲያስቆጥር 38 ጎሎችን አስተናግዷል። 

ቡድኑ በ10 ነጥብ የመጨረሻውን 14ኛ ደረጃን ይዟል።

ተጋጣሚው ኢትዮ ኤሌክትሪክ በውድድር ዓመቱ 21 ጨዋታዎችን አከናውኖ በ17 ድል ሲቀናው አንድ ጊዜ ተሸንፏል። በቀሪ ሶስት ጨዋታዎች ነጥብ ተጋርቷል። 46 ግቦችን ከመረብ ላይ ሲያሳርፍ 11 ጎሎች ተቆጥረውበታል።

ኢትዮ ኤሌክትሪክ በ54 ነጥብ ሁለተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል። 

አርባምንጭ ከተማ ድል ከቀናው ቡድኑ ከወራጅ ቀጠና ለመውጣት በሚያደርገው ትግል ወሳኝ ሶስት ነጥብ ያስገኝለታል።

ኢትዮ ኤሌክትሪክ ካሸነፈ በዋንጫ ፉክክሩ ወሳኝ ሶስት ነጥብ ያገኛል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም