በክልሉ በከተማና ገጠር ወረዳዎች የህዝቡን ተጠቃሚነት እያጎለበቱ የሚገኙ ተግባራት ተጠናክረው ይቀጥላሉ - ኢዜአ አማርኛ
በክልሉ በከተማና ገጠር ወረዳዎች የህዝቡን ተጠቃሚነት እያጎለበቱ የሚገኙ ተግባራት ተጠናክረው ይቀጥላሉ
ሐረር፤ ሚያዝያ 16/2018(ኢዜአ)፦ በሐረሪ ክልል በከተማና ገጠር ወረዳዎች የህዝቡን ተጠቃሚነት እያጎለበቱ የሚገኙ ተግባራት ተጠናክረው እንዲቀጥሉ በትኩረት እንደሚሰራ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ኦርዲን በድሪ አስታወቁ።
የሐረሪ ክልል መንግስት አስፈጻሚ አካል የበጀት ዓመቱ ዘጠኝ ወራት የሥራ አፈጻጸም ግምገማ ተጠናቅቋል።
በግምገማ መድረኩም የአስፈጻሚው አካላት የበጀት ዓመቱ ዘጠኝ ወራት የስራ አፈጻጸም ሪፖርት ቀርቦ ሰፊ ውይይት ተካሄዷል።
የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ኦርዲን በድሪ በመድረኩ ማጠቃለያ እንደገለጹት በበጀት ዓመቱ ዘጠኝ ወራት በሁሉም ዘርፎች በተከናወኑ ተግባራት አበረታች ውጤቶች ተመዝግበዋል።
በተለይ በክልሉ ከተማና ገጠር ወረዳዎች ለህዝቡ ጥያቄዎች ምላሽ የሰጡና ተጠቃሚነትን ያሳደጉ ተግባራት መከናወናቸውን አንስተዋል።
እንዲሁም በአመራሩ በኩል በክልሉ ለሚከናወኑ ቀጣይ ተግባራት ተነሳሽነትን ያጎለበቱ መሆናቸውን ጠቁመው ተግባራቱ ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ አመላክተዋል።
የተከናወኑት ተግባራት አበረታች ቢሆንም የአፈጻጸም ክፍተት የታየባቸው አንድ አንድ ተግባራትን በቀጣይ ሶስት ወራት በአግባቡ መፈጸም እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
በተሻለ ፍጥነትና ጥራት እንዲሁም በተቀናጀ መልኩ ስራዎችን በማከናወን የህዝቡን እርካታ ማጎልበት እንደሚገባ አሳስበዋል።
እንዲሁም የአፈጻጸም ቁርጠኝነትን በማጎልበት፣ ቅንጅታዊ አሰራርን በማጠናከርና የጋራ ግብን በመሰነቅ የተጀመሩ የልማት፣ የሰላም፣ የመልካም አስተዳደርና ሌሎች ተግባራትን በበለጠ ስኬታማ ማድረግ ይገባል ብለዋል።