ቀጥታ፡

ለአረንጓዴ አሻራ ልማት ስኬት የሚዲያና ኮሙኒኬሽን ባለሙያዎች ሚና ላቀ ነው

ሆሳዕና ፤ ሚያዝያ 16/2018 (ኢዜአ)፦ከአካባቢ ጥበቃ ባለፈ ለምግብ ዋስትና መሰረት ለሆነው የአረንጓዴ አሻራ ልማት ስኬት የሚዲያና ኮሙኒኬሽን ባለሙያዎች የላቀ ሚናቸውን ማስቀጠል እንዳለባቸው የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ግብርና ቢሮ ገለጸ፡፡

የክልሉ ደንና አካባቢ ጥበቃ ልማት ቢሮ ከክልሉ የመንግሥት ኮሙኒኬሽን ቢሮ ጋር በመተባበር በአረንጓዴ አሻራ ልማት ዙሪያ ለሚዲያና ኮሙኒኬሽን ባለሙያዎች በሆሳዕና ከተማ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠና ሰጥቷል፡፡


 

በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የገጠር ልማት ክላስተር አስተባባሪና የክልሉ ግብርና ቢሮ ኃላፊ ኡስማን ሱሩር እንደገለጹት፤ በክልሉ የአረንጓዴ አሻራ ትግበራ ከደን ልማቱ ባለፈ የስነ ምግብ ዋስትና መሰረት እየሆነ መጥቷል።

በልማቱ ዘርፈ ብዙ አገልግሎት ያላቸውንና ለምግብ የሚሆኑ የፍራፍሬ ተክሎችን በብዛትና በስፋት የማልማት ሥራ እየተከናወነ መሆኑን ገልጸዋል።

በመሆኑም ለተፈጥሮ ሃብት ጥበቃና ለምግብ ዋስትና መሰረት ለሆነው የአረንጓዴ አሻራ ልማት ስኬት የሚዲያና ኮሙኒኬሽን ባለሙያዎች ሚናቸውን አጠናክረው ሊቀጥሉ እንደሚገባ አንስተዋል።

የስልጠናው ዓላማም የሚዲያና ኮሙኒኬሽን ባለሙያዎች በእውቀትና መረጃ ላይ የተመሰረተ መረጃ ለህዝብ ተደራሽ ማድረግ እንዲችሉ መሆኑን ገልጸዋል።


 

የክልሉ የመንግሥት ኮሙኒኬሽን ቢሮ ኃላፊ ዘሪሁን እሸቱ፤ የሚዲያና ኮሙኒኬሽን ባለሙያዎች በዘርፉ እየተከናወኑ ያሉ የልማት ሥራዎችን በሚገባ ተገንዝበው የተሟላ መረጃ ለህዝብ ተደራሽ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል ብለዋል።

ለዚህም መሰል የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎች ወሳኝ እንደሆኑ አንስተው በቀጣይም በሙያቸው የሚያደርጉትን አስተዋጽኦ በማስቀጠል ልማቱን እንዲያጠናክሩ አስገንዝበዋል።

በመርሐ ግብሩ ላይ የተለያዩ የሚዲያ ተቋማት፤ የኮሙኒኬሽን አመራሮችና ባለሙያዎች እንዲሁም ሌሎች ባለድርሻ አካላት ተሳትፈዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም