በሚቀጥሉት አስር ቀናት የበልግ ዝናብ ተጠቃሚ በሆኑ የሀገሪቱ አካባቢዎች የተሻለ የእርጥበት ሁኔታ ይኖራቸዋል - ኢዜአ አማርኛ
በሚቀጥሉት አስር ቀናት የበልግ ዝናብ ተጠቃሚ በሆኑ የሀገሪቱ አካባቢዎች የተሻለ የእርጥበት ሁኔታ ይኖራቸዋል
አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 16/2018(ኢዜአ)፦ በሚቀጥሉት አስር ቀናት የበልግ ዝናብ ተጠቃሚ በሆኑ የሀገሪቱ አካባቢዎች የተሻለ የእርጥበት ሁኔታ እንደሚኖር የኢትዮጵያ ሚቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት አስታወቀ፡፡
የኢትዮጵያ ሜቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት በሚቀጥሉት አስር ቀናት የሚኖረውን የአየር ሁኔታ ትንበያ አስመልክቶ ለኢዜአ መግለጫ ልኳል፡፡
በዚህም በሚቀጥሉት አስር ቀናት በርካታ የሀገሪቱ አካባቢዎች የተሻለ የእርጥበት ሁኔታ እንደሚያገኙ አመላክቷል፡፡
በመግለጫው በደቡብ የሀገሪቱ ክፍል፣ የስምጥ ሸለቆና አጎራባች አካባቢዎች፣ መካከለኛው፣ ሰሜን ምስራቅ እና ደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ እንዲሁም ሰሜን ምዕራብ እና ምዕራብ የሀገሪቱ አካባቢዎች የተሻለ የእርጥበት ሁኔታ እንደሚኖራቸው አስታውቋል፡፡
በእነዚህ አካባቢዎች የሚኖረው ከመካከለኛ እስከ ከባድ መጠን ያለው ዝናብ ለቋሚ ተክሎች ዕድገት፣ ለግጦሽ ሳርና ለውሃ አቅርቦት መሻሻል ከፍተኛ ፋይዳ እንዳለው ገልጿል።
በሌላ በኩል ከዝናቡ ጋር ተያይዞ የመሬት መንሸራተት፣ የአፈር መሸርሸር እና ድንገተኛ ጎርፍ አደጋዎች ሊከሰት ስለሚችል ጥንቃቄ ማድረግ ይገባል ብሏል፡፡
በተጨማሪም በተደፋታማ ማሳዎች ላይ ውሃ መተኛት፣ የሰብል በሽታና ተባይ መከሰት እንዲሁም የአረም መስፋፋት ሊከሰት እንደሚችል ጠቅሷል፡፡
በዚህም በከተሞች በቆሻሻ የተደፈኑ የውሃ ማፋሰሻ ቱቦዎችን ማጽዳትና የቅድመ ጥንቃቄ ስራዎችን መሥራት ይገባል ብሏል በመግለጫው፡፡
የአፈርና ውሃ እቀባ ስራዎች እንዲሁም የእርከን ስራዎችን ማጠናከር፣ የሰብል በሽታና አረምን አስቀድሞ መከላከል እንዲሁም የእንስሳት መኖ መሰብሰብ እንደሚገባም አመላክቷል፡፡
በተጨማሪም ዝቅተኛ እርጥበት በሚገኝባቸው አካባቢዎች የዝናብ ውሃን በማሰባሰብና ደጋፊ መስኖን በመጠቀም የትነት መጠን የሚያስከትለውን ጉድለት መሙላት እንደሚገባ አስታውቋል፡፡
በአባይ፣ ባሮ አኮቦ፣ የላይኛው ኦሞ ጊቤ፣ ገናሌ ዳዋ እና ስምጥ ሸለቆ ተፋሰሶች ላይ ከአነስተኛ እስከ ከፍተኛ የገፀ-ምድር ውሃ ፍሰት እንደሚኖርም በላከው መግለጫ አስታውቋል፡፡
ይህም ለኃይል ማመንጫ፣ ለመስኖና ለመጠጥ ውሃ አቅርቦት መሻሻል ትልቅ ዕድል እንደሚፈጥር ጠቁሞ፤ ህብረተሰቡ የጎርፍ አደጋን ለመከላከልና የሚገኘውን እርጥበት በአግባቡ መጠቀም እንደሚገባውም አሳስቧል፡፡