ቀጥታ፡

ሀገራዊ ዕቅዶችን በላቀ ውጤት ለመፈጸም ሁሉም አመራር በቀሪ ወራት በፍጥነትና በትኩረት መትጋት ይጠበቅበታል

አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 16/2018(ኢዜአ)፦ በቀሪ ወራት ሀገራዊ ዕቅዶችን በላቀ ውጤት ለመፈጸም ሁሉም አመራር በፍጥነትና በትኩረት መትጋት እንደሚጠበቅበት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ አሳሰቡ።

የ2018 በጀት ዓመት የሦስተኛው 100 ቀን የሥራ አፈጻጸም ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ እና የፌዴራል ተቋማት ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች በተገኙበት ተገምግሟል።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ በዚህ ወቅት መንግሥት በወሰዳቸው የጠራ የፖሊሲ እርምጃዎች በፖለቲካ፣ በኢኮኖሚ፣ በዲፕሎማሲና በሌሎች መስኮች ትላልቅ ስኬቶች መመዝገባቸውን ገልጸዋል።


 

​በኢኮኖሚው ረገድ በሁሉም ዘርፎች እመርታ መምጣቱን ጠቅሰው፥ የአረንጓዴ ዐሻራ፣ የስንዴ ልማት፣ የሌማት ትሩፋት መርኃ ግብሮች የምግብ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ ወሳኝ ሚና እየተጫወቱ ነው ብለዋል።

የገበታ ፕሮጀክቶችና የኮሪደር ልማት ለሀገር ገፅታ መለወጥ፣ ለቱሪዝም ማደግና ለከተሞች ምቹነት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማድረጋቸውን አንስተዋል።

በዲጂታል ዘርፍና በመሶብ የአንድ ማዕከል የመንግሥትን አገልግሎቶች በማዘመን በኩል ለውጥ ማምጣቱን ገልጸዋል።

ባለፉት ስምንት ዓመታት ኢትዮጵያ የተደቀኑባትን ትላልቅ ፈተናዎችና የተከማቹ ዕዳዎችን በመሻገር የከፍታ ምዕራፍ ላይ መድረሷንም ተናግረዋል።

ከለውጡ በፊት በሕዝቡ ዘንድ የአፈጻጸም ድክመት ማሳያ የሆኑ የመንግሥት የልማት ፕሮጀክቶች፥ የጥራት ጉድለት፣ የበጀት ብክነት፣ የጊዜ መዘግየት ምሳሌዎች ሆነው መቆየታቸውን አውስተዋል።

ሀገራዊ ለውጡ ይህን ግዙፍ ችግር ማስወገዱን በማንሳት፥ አሁን ላይ ማንኛውም ፕሮጀክት ሳይገመገምና ሳይጠናቀቅ ወደ አዲስ ሥራ የማይገባበት ጥብቅ ሥርዓት መዘርጋቱን አረጋግጠዋል።

የመደመር መንግሥት ፕሮጀክቶችን ጀምሮ በፍጥነትና በጥራት በመፈጸም የሚታወቅ ሆኗልም ነው ያሉት።

የመካከለኛ እና የአጭር ጊዜ የልማት ዕቅዶች እንዲሁም የሪፎርም ሥራዎች በጥብቅ ዲሲፕሊን እንዲመሩ እየተደረገ መሆኑን ጠቅሰው፥ ለዚህም የአንድ ዕቅድ አንድ ሪፖርት ሥርዓት መዘርጋቱን ገልጸዋል።


 

በመድረኩ የሦስተኛውን የ100 ቀናት አፈጻጸም ሪፖርት ያቀረቡት የፕላንና ልማት ሚኒስትር ዴኤታ በረከት ፍስሐፅዮን በበኩላቸው፥ ከሀገራዊ ለውጡ ወዲህ ሀገራዊ ኢኒሼቲቮችንና ፕሮጀክቶችን በዕቅድ የመፈጸምና የመከታተል ባህል ዳብሯል ብለዋል።

በተለይም የአንድ ዕቅድ አንድ ሪፖርት ሥርዓት መኖሩ መንግሥት ለሕዝብ የገባውን ቃል መተግበሩን በመከታተል የላቀ አፈጻጸም ለማስመዝገብ ትልቅ ለውጥ አምጥቷል ነው ያሉት።

በመድረኩ የተሳተፉ አመራሮች በሰጡት አስተያየት፥ ባለፉት ዓመታት ፈጠራን መሠረት ያደረገና ፈተናዎችን የተሻገረ የተቀናጀ አሠራርን በመከተል በሁሉም መስክ ስኬት መመዝገቡን ገልጸዋል።

በብዝሃ የኢኮኖሚ ዕድገት፣ በዲጂታል፣ በሰብዓዊ ድጋፍና የምግብ ሉዓላዊነት የመጡ ለውጦች ለፈተናዎች የማትበገር ሀገር ለመገንባት ጠንካራ መሠረት ሆነዋል ነው ያሉት።


 

​ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ በሰጡት ማጠቃለያ እስካሁን የተመዘገቡ ስኬቶችን በላቀ ውጤት ማስቀጠል መትጋት ወሳኝ መሆኑን አፅንኦት ሰጥተዋል።

በተለይም መንግሥት በአምሥት ዓመታት ሊፈጽማቸው ለሕዝብ ቃል የገባቸውን ተልዕኮዎች ማሳካት ከሁሉም አመራር እንደሚጠበቅ አስገንዝበዋል።

ለዚህም በሁሉም ዘርፎች በፍጥነት፣ በትኩረትና በትጋት ለላቀ ድል መሥራት ወሳኝ መሆኑን አሳስበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም