በክልሉ ባለፉት ዘጠኝ ወራት ከ302 ኪሎ ግራም በላይ ወርቅ ለብሔራዊ ባንክ ቀርቧል - ኢዜአ አማርኛ
በክልሉ ባለፉት ዘጠኝ ወራት ከ302 ኪሎ ግራም በላይ ወርቅ ለብሔራዊ ባንክ ቀርቧል
ቦንጋ፤ ሚያዝያ 16/2018 (ኢዜአ)፦በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ባለፉት ዘጠኝ ወራት ከ302 ኪሎ ግራም በላይ ወርቅ ለብሔራዊ ባንክ መቅረቡን የክልሉ ማዕድንና ኢነርጂ ልማት ኤጀንሲ አስታወቀ።
ከኢዜአ ጋር ቆይታ ያደረጉት የክልሉ ማዕድንና ኢነርጂ ልማት ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር ጌታቸው ወልያብ (ዶ/ር) እንደገለጹት፤ በክልሉ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ለወርቅና ለድንጋይ ከሰል ልማት ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ ነው።
በበጀት ዓመቱም ከክልሉ 350 ኪሎ ግራም ወርቅ ለብሔራዊ ባንክ ለማቅረብ ታቅዶ ባለፉት ዘጠኝ ወራት ከ302 ኪሎ ግራም በላይ ወርቅ መቅረቡን ገልጸዋል።
የወርቅ ምርቱን 338 ማህበራት እና ግለሰቦች በዘመናዊና ባህላዊ መንገድ እንዳመረቱት ገልጸዋል፡፡
እንደ ዋና ዳይሬክተሩ ገለጻ፣ በዘጠኝ ወር ውስጥ በወርቅ ምርት ለሚሰማሩ 202 አዲዲስ ማህበራትም ፍቃድ ተሰጥቷል።
የተጠናከረ የድጋፍና ክትትል ሥራ መከናወኑ፣ የወርቅ ምርት ያለባቸው አዳዲስ አካባቢዎች ወደሥራ መግባት እና በዘርፉ ህገ-ወጥነትን ለመከላከል የተሰሩ ስራዎች ለወርቅ ምርቱ መሻሻል ምክንያት መሆናቸውን አንስተዋል።
የግብይት ማዕከላት መጠናከርና አቅም ያላቸው ባለሀብቶች በዘርፉ መሰማራታቸው ትልቅ አስተዋፅኦ ማድረጉንም የኤጀንሲው ዳይሬክተር ጌታቸው (ዶ/ር) ጠቁመዋል።
የድንጋይ ከሰል በክልሉ በሰፊው የሚመረት ሌላው ማዕድን መሆኑን ጠቁመው፣ በዘጠኝ ወሩ 150 ሺህ ቶን ለማምረት ታቅዶ እስካሁን ከ122 ሺህ ቶን በላይ ማምረት ተችሏል ብለዋል።
በቀጣይም በክልሉ የማዕድን ሀብት ላይ ጥናት በማድረግ ልማቱን በስፋት አጠናክሮ ለማስቀጠልም እንቅስቃሴ መጀመሩን ገልፀዋል።