መሶብ የአንድ ማዕከል ተንቀሳቃሽ አገልግሎት ፈጣን እና ጊዜ ቆጣቢ ነው- ተገልጋዮች - ኢዜአ አማርኛ
መሶብ የአንድ ማዕከል ተንቀሳቃሽ አገልግሎት ፈጣን እና ጊዜ ቆጣቢ ነው- ተገልጋዮች
አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 16/2018 (ኢዜአ)፦መሶብ የአንድ ማዕከል ተንቀሳቃሽ አገልግሎት ወደ እኛ ከመቅረቡም ባለፈ ፈጣን እና ጊዜ ቆጣቢ ሆኖ አግኝተነዋል ሲሉ ኢዜአ ያነጋገራቸው ተገልጋዮች ገለጹ።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የአገልግሎት ቅልጥፍናንና ተደራሽነትን ለማሻሻል ከፍተኛ ፋይዳ ይኖረዋል ተብሎ የታመነበትን መሶብ የአንድ ማዕከል ተንቀሳቃሽ አገልግሎት በይፋ መርቀው ሥራ ማስጀመራቸው ይታወቃል።
በምረቃው ወቅት ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንደገለጹት፤ ቴክኖሎጂን ለአገልግሎት ዘርፉ እንደ ዋነኛ መሣሪያ በመጠቀም ዜጎች ጊዜ ቆጣቢ አገልግሎት እንዲያገኙ ለማስቻል በቁርጠኝነት እየተሠራ ይገኛል።
የመሶብ የአንድ ማዕከል የአገልግሎት አሰጣጥ ሥርዓት አጭር ጊዜ ቢሆንም፤ በአገልግሎቱ የታየው ከፍተኛ የደንበኞች እርካታ የሥራ ሞዴሉን ውጤታማነት በተግባር ማረጋገጡንም ጠቁመዋል።
መሶብ የአንድ ማዕከል ተንቀሳቃሽ አገልግሎት በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ጀርመን አደባባይ አካባቢ ለህዝቡ አገልግሎት እየሰጠ ይገኛል።
በዚሁ ወቅት ኢዜአ ያነጋገራቸው ተገልጋዮች አገልግሎቱ ፈጣን እና ጊዜ ቆጣቢ መሆኑን ተናግረዋል።
አቶ ኢብራሂም መሐመድ የመኪና ቦሎ ለማደስ ወደ ቦታው መሄዳቸውን ጠቁመው፤ በአጭር ጊዜ ውስጥ ጉዳያቸውን ጨርሰው መመለሳቸውን ተናግረዋል።
አቶ ብስራት ኮሬ እና አቶ ዘላለም አስረስም ለመንጃ ፈቃድና ለቦሎ ዕድሳት ወደ ተንቀሳቃሽ አውቶቡሱ በማቅናት፣ በአይነቱ ልዩና ቀልጣፋ መስተንግዶ ማግኘት መቻላቸውን ተናግረዋል።
ያለምንም ስጋት ጊዜያቸውንም ቆጥበው በአገልግሎቱ ተጠቃሚ በመሆናቸው መደሰታቸውን ይናገራሉ።
በተንቀሳቃሽ አገልግሎቱ ውስጥ የሚሰሩት የገቢዎች ባለሙያ ጫልቱ ታደሰ፣ ይህ አሰራር የተለመደውን በአንድ ቦታ ተወስኖ የመስራት አካሄድ በመቀየር ለተገልጋዩ ብቻ ሳይሆን ለአገልጋዩም ከፍተኛ የስራ ተነሳሽነትን የሚፈጥር መሆኑን ገልጸዋል።
የንግድ ምዝገባ እና ፍቃድ ባለሙያ ብርሃኑ ፈንታው በበኩላቸው፣ ወደ ተገልጋዮች ቀርበው በቴክኖሎጂ የታገዘ ፈጣን አገልግሎት በመስጠት የመጀመሪያዎቹ ባለሙያዎች በመሆናቸው የተሰማቸውን ደስታ ገልጸዋል።
የንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ዋና ስራ አስፈጻሚ ካባ መብራቱ፤ የመሶብ ተንቀሳቃሽ አገልግሎት ቀደም ሲል በሕዝብ ዘንድ ይነሳ የነበረውን ቅሬታ ለመፍታት መንግሥት የወሰደውን ቁርጠኛ አቋም የሚያሳይ መሆኑን ገልጸዋል።
አዲሱ እሳቤ አገልግሎትን ከቢሮ በማውጣት ወደ ሕዝብ ይዞ የመጣ ድንቅ አሠራር መሆኑን አረጋግጠዋል።