ቀጥታ፡

የጤና መረጃ አያያዝና ትንተና ሥርአትን በማዳበር ወረርሽኞችን ቀድሞ ለመከላከል እየተሰራ ነው

ባህር ዳር፤ ሚያዝያ 16/2018 (ኢዜአ)፦የጤና መረጃ አያያዝና ትንተና ሥርአትን በማዳበር የሚከሰቱ ወረርሽኞችን ቀድሞ ለመከላከል እየተሰራ መሆኑን የኢትዮጵያ ሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት አስታወቀ።

በአማራ ክልል ለሞት የሚዳርጉ በሽታዎችን መረጃ አያያዝና አጠቃቀም ላይ ያተኮረ የውይይት መድረክ ዛሬ በባህር ዳር ከተማ ተካሂዷል።

በኢትዮጵያ ሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ብሔራዊ የመረጃ ትንተናና ቅመራ አስተዳደር ማዕከል ዳይሬክተር ዶክተር ትዕግስት ሹመት በመድረኩ እንደገለጹት፤ የጠራ መረጃ ለጤናው ዘርፍ ዕቅድና አፈጻጸም ስኬት አስፈላጊ ነው።


 

የጤና መረጃዎችን በመሰብሰብ፣ በማደራጀትና በመተንተን የሚከሰቱ ወረርሽኞችን ቀድሞ ለመከላከልና ለምርምር ሥራ ለማዋል እየተከናወኑ ያሉ ተግባራት የሚበረታቱ ናቸው ብለዋል።

ይህም እንደሀገር ጠንካራ የመረጃ ሥርዓት በመገንባት በትክክለኛ መረጃ ላይ ተመስርቶ በሽታን ለመከላከል፣ ታማሚዎችን አክሞ ለማዳንና የጤና ግብአትን ለማሟላት ወሳኝ መሆኑን አስገንዝበዋል።

በተለይም የሞትና የጽኑ ሕመም መንስኤዎችን በመለየት ዘላቂ መፍትሄ ለማስቀመጥ "የናሙና ምዝገባ ስርዓት" (SRS) የተባለውን ሳይንሳዊ ዘዴ በሀገር አቀፍ ደረጃ ተግባራዊ ለማድረግ እየተሰራ ነው ብለዋል።

የዛሬው መድረክም በመረጃ አያያዝ ሥርአት ላይ እየተሰራ ያለውን ሥራ ለዘርፉ ባለሙያዎችና አመራሮች በማስገንዘብ በቀጣይ ትኩረት ሰጥተው እንዲሰሩ ለማድረግ ያለመ መሆኑንም አስታውቀዋል።


 

የአማራ ክልል ሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር አቶ በላይ በዛብህ በበኩላቸው እንዳሉት፤በጤናው ዘርፍ የተቀመጡ ግቦችን ለማሳካት የጤና መረጃ አያያዝና ትንተና አስተዳደር ማዕከል ተቋቁሞ ወደ ስራ ገብቷል። 

ማዕከሉ በክልሉ የ25 ዓመት የጤና ዘርፍ አሻጋሪ ስትራቴጂክ ዕቅድን በተሟላ ሁኔታ በመተግበር ጤናማና አምራች ዜጋ ለመፍጠር ጠቀሜታው የጎላ መሆኑንም አስረድተዋል።

ማዕከሉም ጥሬ መረጃን ከመሰብሰብ ባለፈ መረጃው በሚመነጭበት ቦታ ላይ ሳይንሳዊ ትንተና በመስራት አፋጣኝ ምላሽ ለመስጠት እንደሚያስችልም ተናግረዋል። 

በባህር ዳር ከተማ በተካሄደው መድረክ ላይ የፌዴራልና የክልል የዘርፉ ባለሙያዎችና አመራሮች ተሳትፈዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም