ቀጥታ፡

የፀደቁ ደረጃዎች በዓለም አቀፍ ንግድ ተቀባይነትን መጨመር ያስችላሉ

አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 16/2018(ኢዜአ)፦ በምግብ፣ በግብርና እንዲሁም በኮንስትራክሽንና ሲቪል ምህንድስና ዘርፎች የፀደቁ ደረጃዎች፣ በዓለም አቀፍ ንግድ ተቀባይነትን ከመጨመር ባለፈ የገቢ ምርቶች ጥራት ቁጥጥር ወጥ እና አስተማማኝ እንዲሆን እንደሚያስችሉ የኢትዮጵያ የደረጃዎች ኢንስቲትዩት ገለፀ።

ኢንስቲትዩቱ በምግብ፣ በግብርና እንዲሁም በኮንስትራክሽንና ሲቪል ምህንድስና ዘርፎች ላይ ያተኮሩ 66 ደረጃዎችን አጽድቋል፡፡

እነዚህ ደረጃዎች የሀገሪቱን ምርቶች በዓለም አቀፍ የንግድ ሥርዓት ውስጥ ተወዳዳሪ ለማድረግና የገቢ ምርቶችን ጥራት ለመቆጣጠር ጉልህ ሚና እንደሚኖራቸው ተገልጿል።

ኢንስቲትዩቱ በምግብ ጨው ላይ የሚደረግ የደብል ፎርቲፊኬሽንን እንዲሁም ግንባታዎች ከንፋስና መሬት መንቀጥቀጥ አደጋ የመከላከል አቅማቸውን የሚያሳድጉ ዘመናዊ የኮንስትራክሽን ቴክኖሎጂ ደረጃዎች በቦርድ መጽደቃቸውን አስመልክቶ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥቷል፡፡

የኢንስቲትዩቱ የሕዝብ ግንኙነትና ኮሚኒኬሽን ሥራ አስፈፃሚ ብሩክ ሀብቴ እንደገለጹት፤ የኢትዮጵያ የደረጃዎች ቦርድ ሚያዝያ 9 ቀን 2018 ዓ.ም ባካሄደው 5ኛ መደበኛ ስብሰባው የቀረቡለትን 66 ደረጃዎች መርምሮ አጽድቋል፡፡

ካጸደቃቸው ደረጃዎች መካከል 24ቱ አዳዲስ ደረጃዎች ሲሆኑ 42ቱ የተከለሱ መሆናቸውን ጠቅሰው ከእነዚህም ውስጥ 54ቱ አስገዳጅ ደረጃዎች ሆነው መጽደቃቸው ጠቁመዋል፡፡

በምግብና ግብርና ዘርፍ የጸደቁት ደረጃዎች በተለይ በዜጎች ጤና ላይ ትኩረት ያደረጉ መሆናቸውን ጠቁመው በምግብ ጨው ላይ ፎሊክ አሲድ ተጨምሮ እንዲመረት የሚያስገድድ አዲስ ደረጃ መጽደቁንም ገልጸዋል፡፡

ይህም በእናቶችና በሕፃናት ላይ የሚስተዋሉ የጤና እክሎችን ለመቅረፍ ታስቦ የተዘጋጀ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

ከኮንስትራክሽን ጋር በተገናኘ የጸደቁት ደረጃዎች ኢትዮጵያ አሁን ላይ የደረሰችበትን የህንጻ ግንባታ እድገትና ዓለምአቀፍ የቴክኖሎጂ ሽግግርን ያገናዘቡ ናቸውም ብለዋል።

ግንባታዎች ከንፋስና ከመሬት መንቀጥቀጥ አደጋዎች የተጠበቁ እንዲሆኑ የሚያስችሉ የቴክኖሎጂ አጠቃቀሞች የተካተቱ መሆናቸውንም ተናግረዋል፡፡

የደብል ፎርቲፊኬሽንና ዘመናዊ የግንባታ ግብአቶችን በመጠቀም የግንባታዎችን የጥራት ደረጃ ማረጋገጥ የሚያስችሉ መመሪያዎች መቀመጣቸውንም ነው የጠቆሙት፡፡

ደረጃዎቹ መጽደቃቸው ለኢኮኖሚ ዕድገት፣ ለምርምር፣ ለእውቀት ሽግግርና ለሸማቾች መብት መከበር ትልቅ አስተዋጽኦ እንዳላቸውም ገልጸዋል።

የሀገር ውስጥ ምርቶች በዓለም ገበያ ተቀባይነት እንዲኖራቸውና የገቢ ምርቶች ጥራት ወጥ በሆነ መንገድ እንዲፈተሹ የሚያስችል መሆኑንም አክለዋል፡፡

በተጨማሪም የዜጎችን ደህንነትና የአካባቢ ጥበቃን እንደሚያረጋግጥም አቶ ብሩክ ሀብቴ አስታውቀዋል፡፡

አምራቾችና አስመጪዎች የወጡትን ደረጃዎች አውቀው ምርቶቻቸውን በደረጃው መሠረት እንዲያቀርቡና ጥራታቸውን በማሻሻል ለዜጎች ደህንነትና ለሀገር ገጽታ ግንባታ የበኩላቸውን እንዲወጡ ኢንስቲትዩቱ ጥሪ አቅርቧል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም