ለመጪው የመኸር ወቅት ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ ርብርብ ይደረጋል - ኢዜአ አማርኛ
ለመጪው የመኸር ወቅት ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ ርብርብ ይደረጋል
ደብረ ብርሃን፤ ሚያዝያ 16/2018 (ኢዜአ)፦ በሰሜን ሸዋ ዞን ለመጪው የመኸር ወቅት ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ የምግብ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ ለተያዘው ግብ ስኬት ርብርብ የሚደረግበት መሆኑን የዞኑ ግብርና መምሪያ አስታወቀ።
መምሪያው ባለድርሻ አካላትን ያሳተፈ የ2018/19 የመኸር ሰብል ልማት የእቅድ ትውውቅ የንቅናቄ መድረክ በደብረ ብርሃን ከተማ ዛሬ አካሄዷል።
የዞኑ ግብርና መምሪያ ኃላፊ አቶ ታደሰ ማሙሻ በመድረኩ ላይ እንደገለጹት፤ በግብርናው ዘርፍ ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ ለኢንዱስትሪ ግብዓትና ለወጪ ንግድ የሚተርፍ ምርት ለማምረት እየተሰራ ነው።
በዞኑ መጪው የመኸር ወቅት እርሻ ምርትና ምርታማነት በማሳደግ የምግብ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ የተያዘውን ግብ ለማሳካት ርብርብ ይደረጋል ብለዋል።
አርሶ አደሩ የምርት ማሳደጊያ ቴክኖሎጂዎችን፣ አዳዲስ አሰራሮችንና ግብዓትን በመጠቀም የተያዘውን ግብ እንዲያሳካ በየደረጃው ያለው አመራርና ባለሙያ ጠንክሮ የሚሰራ መሆኑን ገልጸዋል።
በዚህም በመጪው የመኸር ወቅት 556 ሺህ ሄክታር መሬትን በዘር በመሸፈን 20 ነጥብ 8 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ለማምረት ታቅዶ ወደ ስራ ተገብቷል ነው ያሉት።
በአሁኑ ወቅት 90 በመቶ የሚሆነውን መሬት እስከ ሶስት ጊዜ ደጋግሞ በማረስ ለዘር ዝግጁ ማድረግ መቻሉን ጠቁመው ከዚህ ውስጥ 52 ሺህ ሄክታር የሚሆነው በሜካናይዜሽን የሚለማ ነው ብለዋል።
ምርታማነትን ለማሳደግም እስካሁን 650 ኩንታል ማዳበሪያ ወደ ዞኑ በማስገባት ለአርሶ አደሩ እየተሰራጨ እንደሚገኝ አስረድተዋል።
ይህም አርሶ አደሩ የምግብ ሉዓላዊነትን ከማረጋገጥ ባሻገር ለገበያ የሚተርፍ ምርት ለማምረት የሚያስችል ሲሆን የዛሬው መድረክም የተጀመሩ ተግባራትን አጠናክሮ በማስቀጠል ግቡን ለማሳካት ያለመ መሆኑን ጠቁመዋል።
በዞኑ የሲያደብርና ዋዩ ወረዳ ግብርና ጽህፈት ቤት የሰብል ልማት ባለሙያ አቶ አንዷለም የሻው እንዳሉት፤ የሞዴል አርሶ አደሮችን ተሞክሮ ወደ ሁሉም አርሶ አደሮች በማሸጋገር ግቡን ለማሳካት ይሰራል።
በምንጃር ሸንኮራ ወረዳ ግብርና ጽህፈት ቤት የሰብል ልማት ባለሙያ አቶ በቀለ ወንድወሰን በበኩላቸው፤ በሙያቸው አርሶ አደሩን በመደገፍ የሚጠበቅበትን ምርት እንዲያመርት እንደሚያደርጉም ገልጸዋል።
በመድረኩ ላይ በዞኑ ስር የሚገኙ የግብርና አመራሮች፣ ባለሙያዎች፣ ከምርምር ተቋማትና ከደብረ ብርሃን ዩኒቨርሲቲ የመጡ ባለድርሻ አካላት ተሳትፈዋል።