ኢትዮጵያ እያካሄደችው ያለው ሪፎርም ለኢንቨስትመንት ምቹ ምህዳር እየፈጠረ ነው - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ እያካሄደችው ያለው ሪፎርም ለኢንቨስትመንት ምቹ ምህዳር እየፈጠረ ነው
አዲስ አበባ፤ሚያዝያ 16/2018 (ኢዜአ)፦ኢትዮጵያ እያከናወነችው ያለው የኢኮኖሚ ሪፎርም፣ምቹና ተገማች የኢንቨስትመንት ምህዳር እየፈጠረ እንደሚገኝ የተባበሩት መንግሥታት የኢንዱስትሪ ልማት ድርጅት (ዩኒዶ) የዘላቂ ኢንቨስትመንትና ማኅበራዊ ኃላፊነት ዘርፍ ኃላፊ ስቴፋን ክራትዝሽ ገለጹ።
ስቴፋን ክራትዝሽ ማሻሻያዎቹ የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንትንና የአገር ውስጥ ካፒታልን ለመሳብ ፋይዳቸው የጎላ መሆኑን ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቆይታ ገልጸዋል።
ይህም ኢንቨስትመንቱ ለሥራ ዕድል ፈጠራ፣ ለእሴት ሰንሰለት ልማትና ለወጪ ንግድ ዕድገት አስተዋጽኦ እንዲያበረክት ያስችላል ብለዋል።
የኢትዮጵያ ሰፊ የሕዝብ ቁጥር ትልቅ የገበያ ዕድል እንደሚፈጥርና ይህም ባለሀብቶች ሥራቸውን በሀገር ውስጥ እንዲያስፋፉ እንዲሁም እንደ የአፍሪካ አህጉራዊ ነፃ የንግድ ቀጣና ባሉ ማዕቀፎች አማካኝነት ወደ ቀጣናዊና አህጉራዊ ገበያዎች እንዲገቡ ዕድል እንደሚሰጥ አመልክተዋል።
የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንትን ከሀገር ውስጥ ኢንዱስትሪ ልማት ጋር ማመጣጠን አስፈላጊ መሆኑን ያመለከቱት ኃላፊው፣ የጋራ ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ እንደ የጋራ ሽርክና እና የመንግሥትና የግሉ ዘርፍ አጋርነቶች አስፈላጊ መሆናቸውን አጽንኦት ሰጥተዋል።
ጠንካራ የአስተዳደር ሥርዓት ያላቸውና በተለይም የሴቶችንና የወጣቶችን የሥራ ዕድል እንዲሁም የውሳኔ ሰጪነት ሚና የሚያረጋግጡ አካታች ኢንቨስትመንቶች ቅድሚያ ሊሰጣቸው እንደሚገባም ነው ያሳሰቡት።
የኢትዮጵያ መንግሥት ከባለሀብቶች ጋር ያለውን ግልጽነትና ትብብር ያደነቁት ኃላፊው፤ የባለሀብቶችን እምነት ለማጠናከርና የንግድ ምህዳሩን ይበልጥ ለማሻሻል በመንግሥትና በግል ዘርፍ መካከል የሚደረገው ውይይት ተጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባ ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ በአህጉሪቱ የኢንዱስትሪ እንቅስቃሴ ውስጥ ግንባር ቀደም ተዋናይ የመሆን ዕድሏ ሰፊ መሆኑንና ለሌሎች የአፍሪካ አገራትም በአርአያነት ልትጠቀስ እንደምትችል አመልክተዋል።
ዩኒዶ የኢትዮጵያን የኢንዱስትሪ ልማት በቴክኒክ፣ በአቅም ግንባታና በፖሊሲ ማማከር እየደገፈ ይገኛል።