በ2018 የበልግ ወቅት እስካሁን ከ840 ሺህ ሔክታር በላይ ማሳ ለምቷል - ኢዜአ አማርኛ
በ2018 የበልግ ወቅት እስካሁን ከ840 ሺህ ሔክታር በላይ ማሳ ለምቷል
ወላይታ ሶዶ፤ ሚያዝያ 16/2018 (ኢዜአ)፡- በዘንድሮው የበልግ ወቅት ከ840 ሺህ ሔክታር የሚልቅ ማሳ በዘር መሸፈኑን የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ግብርና ቢሮ አስታወቀ።
በ2018 የበልግ ወቅት ከ980 ሺህ ሔክታር የሚልቅ ማሳ በማልማት ከ97 ሚሊየን ኩንታል በላይ ምርት ለመሰብሰብ ታቅዶ ወደ ሥራ መገባቱን የቢሮው ምክትልና የእርሻ ዘርፍ ኃላፊ አድማሱ አወቀ ተናግረዋል።
እስካሁንም ለማልማት ከታቀደው ከ840 ሺህ ሔክታር የሚልቀው ማሳ በዘር መሸፈኑን ጠቁመዋል።
ለበልፉ ወቅት ሥራ ከ59 ሺህ በላይ ኩንታል የበቆሎ ምርጥ ዘር እና ከ200 ሺህ ኩንታል በላይ የአፈር ማዳበሪያ ለአርሶ አደሮች መድረሱንም አረጋግጠዋል።
የግብርና ምርታማነትን በማሳደግ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ ለተጀመረው ጥረት የባለሙያ ድጋፍ መጠናከሩንም አመላክተዋል።
በወላይታ ዞን ኪንዶ ኮይሻ ወረዳ የፋጄና ማታ ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር ጀማነህ ጃምቦ፤ ማሳቸውን በትራክተር አርሰው በበቆሎ እና ካሳቫ ዘር መሸፈናቸውን ገልጸዋል።
ምርጥ ዘርና ማዳበሪያ በወቅቱ በመቅረቡ ሥራቸውን በግብርና ባለሙያዎች ታግዘው እየሠሩ መሆናቸውንም አንስተዋል።
በሁምቦ ወረዳ የኮይሻ ኦጎዳማ ቀበሌ አርሶ አደር ደሞዜ ለማ በበኩላቸው፤ በቆሎ እና አደንጓሬ መዝራታቸውን ተናግረው ለሰብላቸው እንክብካቤ በማድረግ የተሻለ ምርት ለማግኘት ማቀዳቸውን ገልጸዋል።
ግብዓቶችን በወቅቱ እንዳገኙ ተናግረው፤ በግብርና ባለሙያዎች አስፈላጊው ሙያዊ ድጋፍ እየተደረገላቸው መሆናቸውንም አክለዋል።