የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ ተኪ ምርት የማምረት አቅማችንን እንድናጎለብት አግዞናል-አምራቾች - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ ተኪ ምርት የማምረት አቅማችንን እንድናጎለብት አግዞናል-አምራቾች
አርባ ምንጭ ፤ሚያዝያ 16/2018(ኢዜአ)፦የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ ተኪ ምርት የማምረት አቅማችንን እንድናጎለብት አግዞናል ሲሉ አምራች እንዱስትሪዎች ገለጹ፡፡
"ሁለንተናዊ ሉዓላዊነት ለኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ" በሚል መሪ ሃሳብ በአርባ ምንጭ ከተማ በተዘጋጀው ክልል አቀፍ ኤግዚቢሽንና ባዛር ላይ የተሳተፉ ኢንዱስትሪዎች በተኪ ምርቶች ያለንን ሚና እንድናጎለብት አስችሎናል ብለዋል።
በክልሉ ጂንካ ከተማ የባስልኤል ኢንጂነርንግ ኢንተርፕራይዝ ሰብሳቢ አቶ ጌታቸው መሃመድ እንዳሉት፤ ችግር ፈቺ የፈጠራ ስራዎችንና ተኪ ምርቶችን በማምረት ማህበረሰቡን ተጠቃሚ እያደረግን እንገኛለን።
በዚህም የውሃ ጉድጓድ መቆፈሪያን ጨምሮ የቡና መቁያና መፍጫ እንዲሁም የገብስ መፈተጊያ ማሽኖችን እያመረትን ነው ብለዋል።
በተለይ በውሃ ጉድጓድ መቆፈሪያ ማሽን በከተማው ከ100 በላይ የውሃ ጉድጓዶችን በመቆፈር ህብረተሰቡን ተጠቃሚ ማድረጋቸውን ነው የተናገሩት።
ድርጅታቸው የትራክተር መለዋወጫ ዕቃዎች ማለትም ማረሻዎች፣ መከስከሻዎችና ሌሎች ከውጭ ገብተው ከሚሸጡበት ከ100 እስከ 300 ሺህ ብር ቅናሽ በማድረግ የዶላር ምንዛሬ ጫናን መቅረፍ ችለናል ብለዋል።
የሴቶችን ጊዜና ጉልበት የሚቆጥቡና የስራ ጫና የሚቀንሱ የዳጣ ማላሚያ፣ የአተር መከኪያ፣ የሽንኩርት መፍጫና ሌሎቹ ተኪ ምርቶችን ስለማምረታቸው አብራርተዋል፡፡
ለዚህም በመንግስት እና በከተማ አስተዳደሩ እየተደረገላቸው ያለው ድጋፍ እገዛ ማድረጉን አመልክተዋል፡፡
የአካባቢውን የባህል ሽመና የሀገር በቀል ዕውቀት እሴትን በመጨመር አምርቶ ለሀገር ውስጥና ለዓለም አቀፍ ገበያ እያቀረበ መሆኑን የገለጸው ደግሞ በአርባ ምንጭ የጃኖ ዕደ ጥበብ ኢንተርፕራይዝ ሰብሳቢ ፍሬው ቆንጆ ነው።
ኢንተርፕራይዙ በዋናነት የእጅ ሽመና በመጠቀም ለፋሽንና ለቤት ቁሳቁስ የሚሆኑ የተለያዩ አልባሳትን በማምረት በተኪ ምርት ጉልህ ሚና እየተጫወተ ይገኛል።
የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ ተወዳዳሪ የሆኑ ተኪ ምርቶችን በማምረት የውጭ ምንዛሬን እንድናድን ብሎም ምርቶቻችን እንድናስተዋውቅ ትልቅ እገዛን አድርጎልናል ብሏል።
የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ንግድና ኢንዱስትሪ ቢሮ ኃላፊ ወይዘሮ ሰናይት ሰለሞን፥የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ የኢንዱስትሪዎች የማምረት አቅም እንዲጎለብት አድርጓል ብለዋል።
ንቅናቄው የኢትዮጵያ ምርቶችን ከማስተዋወቅና ተጨማሪ የገበያ ዕድሎችን ከማስፋት ባሻገር የሀገር ውስጥ ምርት አጠቃቀም ላይ ተጨባጭ ለውጥ አምጥቷል ነው ያሉት።
በአርባ ምንጭ ከተማ በተዘጋጀው የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ ኤግዚቢሽንና ባዛር ከ70 በላይ አምራች ኢንዱስትሪዎች በመሳተፍ ምርቶቻቸውን እያስተዋወቁ ይገኛሉ።