ቀጥታ፡

የክልሉ ፖሊስ በሪፎርሙ የክልሉን ሕዝብ ሰላም በአስተማማኝ ሁኔታ ለመጠበቅ የሚያስችል ቁመና ፈጥሯል

ባሕር ዳር፤ ሚያዝያ 16/2018 (ኢዜአ)፡- የአማራ ክልል ፖሊስ በተቋሙ በተከናወነው ሪፎርም የክልሉን ሕዝብ ሰላምና ደኅንነት በአስተማማኝ ሁኔታ ለመጠበቅ የሚያስችል ቁመና መፍጠሩን የክልሉ ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ አስታወቀ።

የተቋሙ ያለፉት ዘጠኝ ወራት የሥራ አፈጻጸም የግምገማ መድረክ በባሕር ዳር ከተማ እየተካሄደ ነው።


 

የክልሉ ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ አዛዥ ኮሚሽነር ጀነራል ዘላለም መንግሥቴ (ዶ/ር) በዚሁ ወቅት እንዳሉት፤ ይስተዋል የነበረውን የሰላም እጦት ችግር በተቀናጀ አግባብ መፍታት እየተቻለ ነው።

በዚህም ባለፉት ወራት በተከናወኑ የሰላም ማስከበር፣ የወንጀል መከላከል፣ የሰው ኃይል ስምሪትና መሰል ተግባራት ውጤታማ ሥራዎችን ማከናወን እንደተቻለ ገልፀዋል።

ባለፈው አንድ ዓመት በፖሊስ ተቋሙ በተካሄደው ሁሉን አቀፍ ሪፎርም የክልሉን ሕዝብ ሰላምና ደኅንነት ማስጠበቅ ያስቻለ ቁመና መፈጠሩን አረጋግጠዋል።

ሪፎርሙ በሰው ኃይል ልማት፣ በቴክኖሎጂ፣ በዲጂታላይዜሽን፣ በመፈፀምና የማስፈፀም ዐቅም እንዲሁም የሰው ኃይል ብቃትን በማሳደግ ተጨባጭ ለውጥ ማምጣቱንም አብራርተዋል።


 

ተቋሙ ባለፉት ዘጠኝ ወራት ከቀረቡ 13 ሺህ የምርመራ መዝገቦች ከ10 ሺህ የሚልቁ መዝገቦችን በመመርመርና በማደራጀት ለዐቃብያነ ሕግ ማቅረብ መቻሉንም አመላክተዋል።

ይህም ትልቅ ለውጥ እንደሆነ አንስተው፤ ድንበር ተሻጋሪ ወንጀሎችን በትብብር በመከላከልም ወንጀለኞችን በቁጥጥር ሥር ለማዋል የሚያስችል ሥርዓት ተፈጥሯል ነው ያሉት።

በክልሉ ያለውን ሰላም ለማጽናት እና የተጀመሩ የልማት ሥራዎች እንዲቀላጠፉም ፖሊስ ውጤታማ ተግባራት ማከናወኑን አጠናክሮ እንደሚቀጥል አመላክተዋል።

እስካሁን በተሠሩ የፀጥታ ማስከበር ሥራዎች የክልሉ ሰላም ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተሻሻለ መምጣቱን ጠቁመው፤ ሕብረተሰቡን ያሳተፉ ሰላምን የማስከበር ተግባራት ተጠናክረው ይቀጥላሉ ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም