በብሔረሰብ አሥተዳደሩ ሥነ-ምኅዳርን መሠረት ያደረጉ ችግኞችን ለመትከል ዝግጅት እየተደረገ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በብሔረሰብ አሥተዳደሩ ሥነ-ምኅዳርን መሠረት ያደረጉ ችግኞችን ለመትከል ዝግጅት እየተደረገ ነው
ሰቆጣ፤ ሚያዝያ 16/2018 (ኢዜአ)፡- በመጪው ክረምት ሥነ-ምኅዳርን መሠረት ያደረጉ ችግኞችን ለመትከል የሚያስችል ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን የዋግኽምራ ብሔረሰብ አሥተዳደር ግብርና መምሪያ አስታወቀ።
በመምሪያው የደን ባለሙያ ታደሠ መሳይ ለኢዜአ እንደገለፁት፤ አሥተዳደሩ ዝናብ አጠር ከመሆኑ ጋር ተያይዞ የተፈጥሮ ሃብት ሥራና የደን ልማት ተግባራት በከፍተኛ ትጋት እየተሠራበት ነው።
በዚህም እስካሁን 3 ነጥብ 7 ሚሊየን ችግኞችን ለተከላ ዝግጁ ማድረግ መቻሉን ጠቁመው፤ ችግኞቹ ምኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ያላቸውና ሀገር በቀል ናቸው ብለዋል።
በበጋው ወራት የአፈርና ውኃ ዕቀባ ሥራ የተሠራበትን ጨምሮ ከ2 ሺህ 130 ሔክታር በላይ መሬት በመለየት የችግኝ መትከያ ጉድጓድ የማስቆፈር ሥራ እየተሠራ መሆኑንም አስረድተዋል።
ባለፉት ዓመታት ሥነ-ምኅዳሩንና የአየር ንብረቱን መሠረት ያደረጉ ችግኞችን በመትከል አካባቢውን ወደ ምርታማነት የመለወጥ ሥራ ውጤት በማሳየቱ፤ ሕብረተሰቡ ለተፈጥሮ ሃብት ሥራ ከፍተኛ ፍላጎት ማሳየቱን ጠቁመዋል።