ቀጥታ፡

ሕገ ወጥ የንግድ እንቅስቃሴን ለመከላከል የቁጥጥር ሥራዎች እየተከናወኑ ነው

ነቀምቴ፤ ሚያዝያ16/2018 (ኢዜአ፡- በምሥራቅ ወለጋ ዞን የኮንትሮባንድ እንቅስቃሴና ሕገወጥ ንግድን ለመከላከል በቅንጅት እየተሠራ መሆኑን የዞኑ የንግድ ጽሕፈት ቤት አስታወቀ።

በዞኑ ሕገ ወጥ የንግድ ተግባር እንዳይስፋፋ ግብረ-ኃይል ተቋቁሞ እየተሠራ መሆኑን የጽሕፈት ቤቱ ተወካይ ኃላፊ ከበደ በንቲ ተናግረዋል።

በዚህም ያልተገባ ዋጋ የጨመሩ 130 ነጋዴዎችን ለሕግ በማቅረብ አስፈላጊው እርምጃ መወሰዱን ገልጸዋል።

አላስፈላጊ ጭማሪ ባደረጉ ግለሰቦች ላይ በተወሰደ እርምጃም ከ600 ሺህ ብር በላይ ገቢ ተገኝቷል ብለዋል።

በሕገ ወጥ መንገድ ሲጓጓዝ የነበረ ከ3 ሚሊየን ብር በላይ የሚገመት ናፍጣ እና ቤንዚን መያዙንም ጠቅሰዋል።
 
ሕገ ወጥ ተግባራቱ የነዳጅ እጥረቱን በማባባስ በሕብረተሰቡም ሆነ በነጋዴው ላይ ጫና እንዳይፈጥሩ ለመከላከል ከሚመለከታቸው የመንግሥት አካላት ጋር በቅንጅት እየተሠራ መሆኑን አስታውቀዋል።
 
ዘርፉ ሕብረተሰቡን ጨምሮ የሌሎች ባለድርሻ አካላት ተሳትፎ እና ቁርጠኝነት የሚጠይቅ በመሆኑም ቅንጅታዊ ሥራው ይጠናከራል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም