አዲስ አበባን የሳይንስና የፈጠራ ማዕከል ለማድረግ በትኩረት እየተሰራ ነው-ከንቲባ አዳነች አቤቤ - ኢዜአ አማርኛ
አዲስ አበባን የሳይንስና የፈጠራ ማዕከል ለማድረግ በትኩረት እየተሰራ ነው-ከንቲባ አዳነች አቤቤ
አዲስ አበባ፤ሚያዝያ 16/2018 (ኢዜአ)፡- አዲስ አበባን የሳይንስና የፈጠራ ማዕከል የሚያደርጉ ሰፋፊ ስራዎች እየተከናወኑ መሆኑን ከንቲባ አዳነች ገለጹ።
ከንቲባ አዳነች አቤቤ 11ኛውን ከተማ አቀፍ የሳይንስ ፈጠራ ስራ አውደ ርዕይ በይፋ ከፍተዋል።
“በሳይንስና ፈጠራ የተካነ ትውልድ ለተምሳሌታዊ ሀገር” በሚል መሪ ሀሳብ የሚደረገው አውደ ርዕይ ዛሬ እና ነገ ክፍት ሆኖ ይቆያል።
ከንቲባዋ አውደ ርዕዩን በከፈቱበት ወቅት ባስተላለፉት መልዕክት፣ መድረኩ የከተማዋን የፈጠራ ጉዞ አንድ ደረጃ የሚያራምድ መሆኑን ገልጸዋል።
የዛሬው የሳይንስ ፈጠራ ስራ አውደ ርዕይ ዋነኛ ዓላማ ተማሪዎች በክፍል ውስጥ በንድፈ ሀሳብ የተማሩትን ትምህርት በተግባር የሚያሳዩበት መድረክ መፍጠር እንደሆነ አመልክተዋል።
አያይዘውም ተማሪዎች የውስጥ ተሰጥዖዋቸውን የሚገልጹበት፣ ለሰሯቸው የፈጠራ ስራዎች ዕውቅናና ማበረታቻ የሚያገኙበት እንዲሁም እርስ በእርስ በትብብር የመስራት ልምድ የሚለዋወጡበት ትልቅ መድረክ ነው ብለዋል።
እውነተኛ እውቀት ችግሮችን ደጋግሞ ማውራት ሳይሆን ለችግሮች መፍትሄ ማፍለቅና ችግርን ወደ ድል መቀየር መሆኑን የጠቀሱት ከንቲባ አዳነች፣ አዲስ አበባን የሳይንስና የፈጠራ ማዕከል ለማድረግ ሰፋፊ ስራዎች እየተሰሩ መሆኑን ጠቁመዋል።
አሁን ላይ የተጀመሩ ስራዎች ውጤት በተጨባጭ መታየት የጀመረበት ወቅት ላይ መደረሱን ገልጸው፣ ይህ ውጤታማ ጅምር ተጠናክሮ እንዲቀጥል ሁሉም ባለድርሻ አካላት ኃላፊነታቸውን በአግባቡ እንዲወጡ ጥሪ አቅርበዋል።
ዛሬ የፈጠራ ስራቸውን ያቀረቡ ተማሪዎችና መምህራን ላይ ትልቅ ተስፋ እንዳላቸው የገለጹት ከንቲባዋ፣ እነዚህ የፈጠራ ስራዎች አድገውና በልጽገው ለከተማዋ፣ለሀገር ብሎም ለዓለም የሚተርፍ በረከት እንደሚሆኑ ያላቸውን እምነት ገልጸዋል።