በጠቅላላ ምርጫው የሴቶችን የመምረጥና የመመረጥን ተሳትፎ የሚያሳድጉ የግንዛቤ ማስጨበጫ ተግባራት እየተከናወኑ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በጠቅላላ ምርጫው የሴቶችን የመምረጥና የመመረጥን ተሳትፎ የሚያሳድጉ የግንዛቤ ማስጨበጫ ተግባራት እየተከናወኑ ነው
አዲስ አበባ፤ሚያዝያ 16/2018 (ኢዜአ)፡- በሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ የሴቶችንና ሌሎች ማህበረሰብ ክፍሎችን የመምረጥና የመመረጥን ተሳትፎ የሚያሳድጉ የግንዛቤ ማስጨበጫ ተግባራትን እያከናወነ መሆኑን የኢትዮጵያ ሲቪል ማህበራት ድርጅቶች ኅብረት ለምርጫ ገለጸ።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የዘንድሮውን ጠቅላላ ምርጫ ከየካቲት 28/2018 ዓ.ም ጀምሮ ሲካሄድ የቆየው የመራጮች ምዝገባ ለተጨማሪ 14 ቀናት ተራዝሞ ሚያዚያ 14/2018 ዓ.ም ምሽት ላይ ተጠናቋል።
ለሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫም 50 ሚሊየን 514 ሺህ በላይ መራጮች በዲጂታልና በምርጫ ጣቢያ በአካል በመገኘት መመዝገባቸውን ቦርዱ ትናንት ሚያዚያ 15/2018 ዓ.ም በሰጠው መግለጫ አስታውቋል።
በቦርዱ የጊዜ ሰሌዳ መሰረት ግንቦት 24/2018 ዓ.ም ድምፅ የሚሰጥ ሲሆን፤ 47 ተፎካካሪ ፓርቲዎችም 10 ሺህ 934 ዕጩዎችን በማስመዝገብ የፖሊሲ አማራጮቻቸውን ለህዝብ በማስተዋወቅ ላይ ይገኛሉ።
የኢትዮጵያ ሲቪል ማህበራት ድርጅቶች ኅብረት ለምርጫ የፕሮግራም አስተባባሪ እዩኤል ዘላለም ለኢዜአ እንዳሉት፤ ምርጫ በአንድ ሀገር ውስጥ በህዝቦች ዘንድ ቅቡልነት ያለው መንግስት መመስረቻ መሳሪያ ነው።
ኅብረት ለምርጫም የኢትዮጵያን 7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ፍትሕዊ፣ ዴሞክራሲያዊና አካታችነት ለማጠናከር የህዝብን ተሳትፎ የሚያሳደግ ድጋፍ እያደረገ መሆኑን ገልጸዋል።
የምርጫ ሂደቱን ዴሞክራሲያዊነት፣ አካታችና አሳታፊነት ለማረጋገጥም የሴቶችንና የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎችን ተሳትፎ የማንቃት ስራ እየሰሩ እንደሚገኝ ተናግረዋል።
በተለይም የሴቶችን የምርጫ ታዛቢነት፣የመምረጥና መመረጥ ተሳትፎን የሚያሳድጉ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠናዎችን በመገናኛ ብዙኅንና በአካል እየሰጡ መሆናቸውን አንስተዋል።
በ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ሂደት ሴቶችንና ሌሎች የማህበረሰብ ክፍሎችን አሳታፊነት ለማረጋገጥም ''እኔ መርጣለሁ'' በሚል መሪ ሃሳብ የመራጮች ትምህርት ዘመቻ መጀመሩንም አስገንዝበዋል።
የሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ ተፎካካሪ ፓርቲዎችም ሴቶች የሚያነሷቸውን ጉዳዮች በፖሊሲ አማራጮቻቸው ላይ ያካተቷቸውን ጉዳዮች በሚገባ ማስተዋወቅ እንደሚኖርባቸው አስረድተዋል።
ይህም ሴቶች ይበጀኛል ለሚሉት የፖለቲካ ፓርቲ ድምፅ የሚሰጡበትን ግንዛቤ ማሳደግ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው ገልጸዋል።
ከባለድርሻ ተቋማት ጋር በመተባበር ለምርጫው ስኬት እየሰሩ መሆኑን ጠቁመው፥ በቀጣይም ሴቶች በምርጫ ሂደት ንቁ ተሳትፎ በማድረግ የሚጠበቅባቸውን ገንቢ ሚና እንዲወጡ ጥሪ አቅርበዋል።