ቀጥታ፡

በሌማት ትሩፋት መርሐ-ግብር የተሰማሩ ወጣቶች ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነታቸው እያደገ ነው

ጎንደር፤ ሚያዝያ 16/2018 (ኢዜአ)፦ በጎንደር ከተማ በሌማት ትሩፋት መርሐ-ግብር በወተት ሀብት ልማት የተሰማሩ ወጣቶች ሀብትና ጥሪት በማፍራት ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነታቸውን ማሳደግ መቻላቸውን ተናገሩ።


 

ወጣት አስናቀ አብተው ለኢዜአ እንደገለጸው፤ በሁለት ላሞች የጀመረውን የወተት ሀብት ልማት ሥራ ይህን አሃዝ አሁን ወደ 17 አሳድጓል።

የሌማት ትሩፋት መርሐ-ግብሩ ሠርቶ መለወጥ የሚለውን ህልሜን ለማሳካት ረድቶኛል፤ በአሁኑ ወቅትም ለዘጠኝ ሰዎች የሥራ ዕድል ፈጥሬያለሁ ብሏል።

በቀን ከ200 ሊትር በላይ ወተት ለገበያ በማቅረብም ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነቱን ማሳደጉን ጠቅሷል።


 

በቀን ከ100 ሊትር በላይ ወተት ለገበያ በማቅረብ ላይ የሚገኘው ወጣት ዓለሙ ሲሳይ በበኩሉ፤ በአንዲት ላም የጀመረውን የወተት ሃብት ልማት ሥራ በአሁኑ ወቅት ወደ ሥድስት የሚታለቡ ላሞች ከፍ አድርጓል።

የሌማት ትሩፋት መርሐ-ግብር የአካባቢ ጸጋዎችን ለይቶ በመጠቀም ከራስ አልፎ ለሌሎችም የሥራ ዕድል በመፍጠር ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነትን የሚያሳድግ መሆኑን በተግባር ማረጋገጡንም ገልጿል።


 

መርሐ-ግብሩ የወጣቱን ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት በተጨባጭ የሚያረጋግጥና በአጭር ጊዜ ሠርቶ መለወጥ እንደሚቻል የሚያመላክት የተግባር ትምህርት ቤት ነው ያለው ደግሞ ወጣት አምሳሉ አካሌ ነው፡፡

በወተት ሀብት ልማት ዘርፍ በመሰማራት ከአራት ላሞቹ የሚያገኘውን የወተት ምርት እሴት ጨምሮ ለገበያ በማቅረብ ራሱንና ቤተሰቡን በተሻለ መንገድ ማኖር እንደቻለም ነው ያመለከተው።


 

የጎንደር ከተማ አሥተዳደር እንስሳትና ዓሣ ሀብት ልማት መምሪያ ኃላፊ መላኩ ደምሌ፤ ባለፉት ሶስት ዓመታት ተግባራዊ የተደረገው የሌማት ትሩፋት መርሐ-ግብር ለወጣቱ ሰፊ  የሥራ እድል ለመፍጠር አስችሏል ብለዋል፡፡

የተሻሻሉ ቴክኖሎጂዎችንና ግብዓቶችን በመጠቀም የወተት ምርትን በማሳደግ በኩል 12 ቴክኒሻኖችን በማሰልጠን ከ14 ሺህ በላይ ላሞችን የማዳቀል ሥራ መከናወኑንም አብራርተዋል።

በወተት ሀብት ልማት ዘርፍ የሚታየውን የእንስሳት መኖ እጥረት ለማቃለል እንዲቻልም በሰአት 30 ኩንታል የእንስሳት መኖ ማዘጋጀትና ማቀናበር የሚችል ዘመናዊ ፋብሪካ ማቋቋም መቻሉን አስረድተዋል፡፡ 


 

በከተማው በወተት ሀብት ልማት፣ በንብ ማነብ፣ በዶሮ እርባታና በእንስሳት ማድለብ እንዲሁም በዓሣ ሀብት ልማት ዘርፍ በክላስተር የተደራጁ ከ25 በላይ ኢንተርፕራይዞች ተቋቁመው ወደ ሥራ መግባታቸውን ጠቁመዋል።፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም